ሰኔ 23, 2022
ዩክሬን
ሕይወቴን ለማትረፍ ያደረግሁት ጉዞ
ከዩክሬን ጦርነት ማምለጥ—አናስታሲያ ኮዝዬኖቫ እንደተናገረችው
የካቲት 24, 2022 ኃይለኛ ድምፅ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። ደጅ ዝናብ እየጣለ ስለነበር መጀመሪያ ላይ የነጎድጓድ ድምፅ መስሎኝ ነበር፤ የሰማሁት ድምፅ የቦምብ ፍንዳታ መሆኑ የገባኝ በኋላ ነው።
ማሪዩፖል ውስጥ መሃል ከተማ የሚገኘውን ቤቴን ለቅቄ መሸሽ ነበረብኝ። በማግሥቱ በከተማው ዳርቻ ወደምትገኘው ወደ አያቴ ኢሪና ቤት ሄድኩ። ብዙም ሳይቆይ እናቴ ካተሪናም መጣች። ለተወሰነ ጊዜ ያህል እኔ፣ እናቴና የአክስቴ ልጅ በአያቴ ቤት ከአደጋው ተሸሽገን ቆየን፤ በእርግጥ ብዙ ጊዜ የምንተኛው ምድር ቤት ውስጥ ነበር።
አንድ ቀን ምድር ቤት ውስጥ እያለን አትክልት ቦታችን ላይ የጦር ሚሳይል ወደቀ። የፍንዳታው ድምፅ ጆሮ የሚያደነቁር ነበር። በዚያ ወቅት ወደ ይሖዋ አጥብቄ ጸለይኩ። ከአንድ ሳምንት በኋላ ግን በአያቴ ቤትም ቢሆን ሁኔታው አደገኛ እንደሆነ ገባን፤ ስለዚህ ወደ መሃል ከተማ ተመልሰን ከከተማዋ የምንወጣበትን መንገድ ብናፈላልግ እንደሚሻል ወሰንን። ይሖዋ ከአደጋ እንዲጠብቀንና ከከተማዋ ለመውጣት እንዲረዳን ተማጸንኩት።
መጋቢት 4 ማለዳ ላይ ወደ መሃል ከተማ ተመለስን። ከተማዋ ተከብባ ስለነበር ከዚያ የሚወጣ ባቡር ማግኘት አልቻልንም። በመሆኑም ለቀጣዮቹ አሥር ቀናት በከተማዋ ቲያትር ቤት ተጠለልን፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚያ ነበሩ። ቲያትር ቤቱ በሕዝብ ስለተጨናነቀ የምንተኛው ወለሉ ላይ ነበር። ቦታው ንጹሕ አልነበረም፤ ምግብና ሙቅ ውኃ ማግኘትም በጣም አስቸጋሪ ነበር። ለሰዓታት ተሰልፈን ወረፋ መጠበቅ ነበረብን።
አንድ ቀን ከቲያትር ቤቱ ብዙም ሳይርቅ ቦምብ ወደቀ። ፍንዳታው በጣም ኃይለኛ ስለነበር ብዙዎቹ መስኮቶች ብትንትናቸው ወጣ፤ በመሆኑም አጥንት ውስጥ የሚገባው ብርድ ያንሰፈስፈን ጀመር።
ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳኝ ምንድን ነው? የኢዮብ ታሪክ። በፍንዳታው የተነሳ ሰዎች በፍርሃት ሲሸበሩ መጽሐፍ ቅዱሴን ከፍቼ የኢዮብን ታሪክ አነብ ነበር። ይህን ማድረጌ እንድረጋጋ ረድቶኛል። እዚያው ቲያትር ቤቱ ውስጥ ኢዮብ አብሮኝ እንዳለ አድርጌ አሰብኩ፤ “ያሳለፍከው ነገር አሁን ነው የገባኝ!” ስለው ታየኝ። ኢዮብ ቤተሰቡን፣ ጤንነቱንና ንብረቱን በአጠቃላይ ያለውን ሁሉ አጥቶ ነበር። እኔ ያጣሁት ቁሳዊ ንብረቶቼን ብቻ ነው። ቤተሰቤ አብረውኝ ናቸው፤ ሁላችንም በሕይወት አለን፤ ጤንነታችንም አልተጓደለም። ይህን ሳስብ፣ ያለንበት ሁኔታ ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ይህም እንድረጋጋ ረዳኝ።
መጋቢት 14 የተወሰኑ ሰዎች ከከተማዋ መውጣት እንደቻሉ ሰማን። ስለዚህ እኛም ለመውጣት ወሰንን። ቲያትር ቤቱ ውስጥ ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር አብረን የምንጓዝበት መኪና አገኘን።
ሃያ መኪኖች በአንድ ላይ ተከታትለው ከከተማዋ ወጡ። እኛ በተጫንንበት የዕቃ ማጓጓዣ መኪና ውስጥ 14 ሰዎች ታጭቀን ነበር። በጉዞ ላይ እያለን በአቅራቢያችን ቦምብ ሲወድቅ ይሰማን ነበር። በወቅቱ ያለማቋረጥ እጸልይ ነበር። ከማሪዩፖል በሰላም ስንወጣ ሹፌሩ መኪናዋን አቁሞ ወረደና ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። መንገዱ ላይ በየቦታው የተቀበሩት ቦምቦች ሳይነኩን በሰላም መውጣት ችለናል። ከማሪዩፖል ከወጣን ከሁለት ቀናት በኋላ ቲያትር ቤቱ በቦምብ እንደተመታና ቢያንስ 300 ሰዎች እንደሞቱ ሰማን።
ከ13 ሰዓታት ጉዞ በኋላ ዛፖሪዢያ ደረሰን። በማግሥቱ ደግሞ ባቡር ተሳፍረን ወደ ልቪቭ አቀናን። ለወትሮው ቢሆን አራት ሰዎች በሚይዘው የባቡሩ ክፍል ውስጥ 16 ሰዎች ተሳፍረው ነበር። በጣም ይሞቅ ስለነበር ሙሉውን ጉዞ ማለት ይቻላል መተላለፊያው ላይ ቆሜ ነበር። ንጹሕ አየር ማግኘት የሚቻለው እዚያ ጋ ብቻ ነበር። መጋቢት 16 ልቪቭ ስንደርስ ወንድሞችና እህቶች ሞቅ አድርገው ተቀበሉን። ለቀጣዮቹ አራት ቀናት በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ቆየን። ወንድሞችና እህቶች ያደረጉልንን እንክብካቤ ሳስበው እንባዬ ይመጣል። ይህ የይሖዋ ስጦታ ነው።
መጋቢት 19 ዩክሬንን ለቅቀን ወደ አጎራባቿ ፖላንድ ለመሄድ ተነሳን፤ ከአያቴ፣ ከእናቴና ከአክስቴ ልጅ ጋር እዚያ ስንደርስ አሁንም የእምነት ባልንጀሮቻችን ተቀበሉን። እንዲሁም የሚያስፈልገንን ሁሉ አሟሉልን። በፍቅር ተንከባከቡን።
ገና 19 ዓመቴ ቢሆንም በዚህ ሁሉ ፈተና በማለፌ አንድ ወሳኝ ትምህርት አግኝቻለሁ፦ በሰላሙ ጊዜ እምነትን መገንባት በጣም አስፈላጊ ነው። መከራን ለማለፍ የሚያስችለን እምነት ነው። ከጦርነቱ በፊት የግል ጥናት ባይኖረኝ ኖሮ ሁኔታዎች በጣም ይከብዱኝ ነበር።
ይሖዋ አሳቢ አባት ነው። በዚህ ሁሉ ጊዜ ቀኝ እጄን ይዞ እየመራኝ እንዳለ ይሰማኝ ነበር። ላደረገልኝ ነገር ሁሉ መቼም ቢሆን ውለታውን መመለስ አልችልም።—ኢሳይያስ 41:10