ጥር 4, 2024
ዩክሬን
መጠበቂያ ግንብ ወደ ዩክሬንኛ መተርጎም ከጀመረ መቶ ዓመታት ተቆጠሩ
መጠበቂያ ግንብ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩክሬንኛ ተተርጉሞ የወጣው የዛሬ 100 ዓመት ነበር። ምሥራቹ በዩክሬን መሰበክ ከጀመረበት ከ1891 አንስቶ ብዙዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት አሥርተ ዓመታት ዩክሬንኛ ተናጋሪ የሆኑ ሌሎች በርካታ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ፍቅር አዳብረዋል። ሆኖም በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ በዩክሬን በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት የዩክሬንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ብዙ ሰዎች ወደ ሌሎች አገሮች፣ በተለይ ደግሞ ወደ ካናዳ እና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰደው ሄዱ።
በ1923 ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ ካናዳን በጎበኘበት ወቅት፣ መጠበቂያ ግንብን ወደ ዩክሬንኛ በመተርጎሙ ሥራ እንዲያግዝ ለወንድም ኤሚል ዛሪስኪ ግብዣ አቀረበለት። ወላጆቹ ከዩክሬን ተሰደው የመጡት ወንድም ኤሚል በወቅቱ ገና ኮልፖርተር (አቅኚ) እና ፒልግሪም (ተጓዥ የበላይ ተመልካች) ሆኖ ማገልገል መጀመሩ ነበር። በዚያ ላይ እሱና ባለቤቱ ማሪያ አምስት ልጆች አሏቸው። ያም ሆኖ ኤሚል የወንድም ራዘርፎርድን ግብዣ ተቀበለ፤ ከዚያም ጥር 1924 የመጀመሪያው ዩክሬንኛ መጠበቂያ ግንብ ወጣ። ኤሚል ለ40 ዓመታት በታማኝነት በትርጉም ሥራ ተካፍሏል። ልጁ ሮዝ “ቤታችን ውስጥ ያለማቋረጥ የሚሰማው የአባባ ታይፕራይተር ድምፅ በደንብ ትዝ ይለኛል” በማለት ያን ጊዜ ታስታውሳለች።
በ1964 ኤሚል መጠበቂያ ግንብን ወደ ዩክሬንኛ በመተርጎሙ ሥራ እንዲያግዙ ወንድም ሞሪስ ሳራንቹክን እና ባለቤቱን አንን አሠለጠናቸው። ወንድም ሞሪስ እና ባለቤቱ በትርጉም ሥራ በቅንዓት ተካፍለዋል፤ እንዲያውም አንዳንዴ ከሰብዓዊ ሥራቸው በሚያርፉበት ጊዜ የመኪናቸው የኋላ ወንበር ላይ ተቀምጠው ይሠሩ ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ባልና ሚስት በአካባቢው ባለ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የምትገኝን አንዲት አነስተኛ ክፍል እንደ ትርጉም ቢሮ እንዲጠቀሙ ዝግጅት ተደረገ። ከዚያም በ1977 በካናዳ ቤቴል እንዲያገለግሉ ተጋበዙ። በጊዜ ሂደት በቅርንጫፍ ቢሮው ያሉ ሌሎች ዩክሬንኛ ተናጋሪ ወንድሞችም መጠበቂያ ግንብን እና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በትክክል መተርጎም እንዲችሉ ሥልጠና ተሰጣቸው።
ከ1940 ጀምሮ ባሉት አሥርተ ዓመታት በሶቪየት ኅብረት ውስጥ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ታግዶ ስለነበር ወንድሞቻችን መጠበቂያ ግንብ እና ሌሎች በዩክሬንኛ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ አገሪቱ ለማስገባት አዳዲስ ዘዴዎችን መጠቀም አስፈልጓቸዋል። በሶቪየት ኅብረት ያሉ ወንድሞች ጽሑፎቹ እንደደረሷቸው ያባዟቸውና ያሰራጯቸዋል፤ በዚህ መንገድ ወንድሞቻችን በጣም የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ ያገኙ ነበር። በመጨረሻም በ1991 የሶቪየት ኅብረት ሲወድቅ በዩክሬን ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በነፃነት አምልኳቸውን ማካሄድ ቻሉ። ከዚያ ብዙም ሳይቆም በጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ የዩክሬንኛ የትርጉም ቡድን ተቋቋመ። በኋላም የትርጉም ቡድኑ ወደ ፖላንድ ተዛወረ፤ ከዚያም በ2001 አዲስ የተገነባው የዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ ሲጠናቀቅ የትርጉም ቡድኑ ወደ ዩክሬን ተዛወረ። ላለፉት 30 ዓመታት በዩክሬንኛ ትርጉም ሥራ የተካፈለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ገና ሥራው በጀመረበት ጊዜ መጠበቂያ ግንብን በመተርጎም፣ በመገልበጥና በማሰራጨት ሥራ የተካፈሉት ወንድሞችና እህቶች በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ለምናየው እድገት አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እነሱ ያሳዩት ቁርጠኝነት አሁንም እንኳ ሥራዬን ሳከናውን ብርታት ይሰጠኛል።”
በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዩክሬንኛ ተናጋሪዎች መጠበቂያ ግንብን በቋንቋቸው በማግኘታቸው ተጠቃሚ ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ በመላው ዩክሬን፣ በዩክሬንኛ የሚካሄዱ 67 ቡድኖችና 541 ጉባኤዎች አሉ። በስሎቫኪያ፣ በስዊድን፣ በስፔን፣ በቤልጅየም፣ በብሪታንያ፣ በቼክ ሪፑብሊክ፣ በአየርላንድ፣ በኦስትሪያ፣ በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በጀርመን፣ በጣሊያን፣ በፈረንሳይ እና በፖላንድም በዩክሬንኛ የሚካሄዱ ቡድኖችና ጉባኤዎች ይገኛሉ።
ይሖዋ መጠበቂያ ግንብ በዩክሬንኛ እንዲዘጋጅ በማድረግ ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች በእሱ ላይ ‘ትምክህታቸውን የሚጥሉበት’ አጋጣሚ በመክፈቱ ምስጋና ይገባዋል።—መዝሙር 78:7