ሚያዝያ 22, 2022
ዩክሬን
“በዚያ ምሽት ይሖዋ እጄን እንደያዘኝና እቅፍ እንዳደረገኝ ተሰማኝ”
ባሎቻቸውን ያጡ የዩክሬን እህቶቻችን በይሖዋ ተስፋዎች ላይ በማሰላሰላቸው ብርታት አግኝተዋል
እህት ልዩድሚላ ሞዙል እና እህት ካተሪና ሮዝዶርስካ ጦርነቱ ካስከተለባቸው አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ሥቃይ ጋር እየታገሉ ነው። የልዩድሚላ ባል የሆነው ፔትሮ ሞዙል እና የካተሪና ባል የሆነው ድሚትሮ ሮዝዶርስኪ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ናቸው። የሚያሳዝነው እስካሁን ድረስ በጦርነቱ የተነሳ 34 ወንድሞችንና እህቶችን አጥተናል።
ፔትሮ እና ልዩድሚላ የተጠመቁት በ1994 ነበር። በትዳር ሕይወት 43 ዓመት አሳልፈዋል።
ልዩድሚላ እንዲህ ብላለች፦ “የእምነት ባልንጀሮቼ በየቀኑ የሚያጽናና ሐሳብ ይነግሩኛል። ያለማቋረጥ ይደውሉልኛል። በዩክሬን ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የደረሰኝ የሚያጽናና ደብዳቤም ልቤን በጥልቅ ነክቶታል።”
ጦርነቱ የጀመረው የካቲት 24, 2022 ነበር። ፔትሮ በምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ነበር። በካርኪቭ ከባድ ፍንዳታ በመኖሩ ምክንያት እሱና ቤተሰቡ መጋቢት 1, 2022 አካባቢውን ለቀው ለመሸሽ ሲሞክሩ ሕይወቱን አጥቷል።
የጦር አውሮፕላኖች ለበርካታ ቀናት ፈንጂ ሲጥሉ ከቆዩ በኋላ በዚያ ዕለት ከከተማዋ በላይ እየበረሩ በከተማዋ ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ። ቤተሰቡ የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገር ብቻ ይዘው በ30 ደቂቃ ውስጥ ቤታቸውን ጥለው ወጡ። ፔትሮ እና ልዩድሚላ በአንድ መኪና ሄዱ። ልጃቸው ኦሌክሲ እና ባለቤቱ ማሪና ደግሞ በሌላ መኪና ሄዱ። ልዩድሚላ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ የመኖሪያ ሰፈር ውስጥ እየሄድን ሳለ አውሮፕላኖቹ ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ። በፍንዳታው የተነሳ መኪናችን ተናወጠ።”
የ67 ዓመቱ ፔትሮ ከኦሌክሲ መኪና ጋር ላለመጋጨት ብሎ መኪናውን ዞር ሲያደርግ ከባድ ጉዳት አጋጠመው። እሱና ልዩድሚላ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ትንሽ ቆይቶ ፔትሮ ሞተ። ልዩድሚላ ከፈንጂው በተፈናጠሩ ብረቶች ምክንያት እግሯና ሆዷ ላይ ጉዳት ደረሰባት። ኦሌክሲና ማሪና ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም። ልዩድሚላ ከሦስት ቀን በኋላ ከሆስፒታል ስትወጣ ፔትሮ መሞቱን ሰማች።
ልዩድሚላ እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ይሖዋ ደግነትና ግሩም ስለሆነው ዓላማው ሳስብ ውስጣዊ ሰላም አገኛለሁ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ባለቤቴን እንደማገኘው እርግጠኛ ነን፤ ያንን ቀን በጉጉት ነው የምጠባበቀው።”
ድሚትሮ እና ካተሪና ስምንት ዓመት በትዳር ቆይተዋል። ድሚትሮ ከመሞቱ በፊት ከሥራ ቦታው ለካተሪና ደውሎ “መጣሁ እሺ” ብሏት ነበር።
መጋቢት 8, 2022 ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የድሚትሮ የሥራ ባልደረባ ለካተሪና ደውሎ ድሚትሮ ፈንጂ በመርገጡ ሆስፒታል እንደገባ ነገራት። ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት ከአምስት ሰዓት በኋላ ሞተ።
ካተሪና፣ ድሚትሮ መሞቱን ከሰማች በኋላ ስለሆነው ነገር ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ ምሽት ይሖዋ እጄን እንደያዘኝና እቅፍ እንዳደረገኝ ተሰማኝ። ይሖዋ እዚሁ ከጎኔ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር።”
የ28 ዓመቱ ድሚትሮ የተጠመቀው በ2006 ሲሆን ዩክሬን ውስጥ በዶኔትስክ ክልል የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል ነበር።
ለድሚትሮ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከተደረገ ብዙም ሳይቆይ ካተሪና ሰላማዊ ወደሆነ የዩክሬን ክፍል ለመሄድ የ12 ሰዓት ጉዞ አደረገች። እንዲህ ብላለች፦ “በመላው ዩክሬንና በሌሎችም አገሮች ከሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ማበረታቻ አግኝቻለሁ። ያሳዩኝ ፍቅር ሥቃዬ ቀለል እንዲለኝ አድርጓል።”
አክላም እንዲህ ብላለች፦ “አገልግሎትም በጣም ያጽናናኛል። . . . ሁኔታው በጣም ሲከብደኝ እንደ ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አነበንባለሁ።”
ይሖዋ በዩክሬን ባለው ጦርነት ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ውድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማበረታታቱንና ማጽናናቱን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—መዝሙር 61:1-3