መጋቢት 3, 2022
ዩክሬን
በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል
የካቲት 24, 2022 ሩሲያ ዩክሬንን ወረረች። ዩክሬን ውስጥ ከ129,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮችና ልጆቻቸው ይኖራሉ። ቅርንጫፍ ቢሮው ለወንድሞቻችን ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ሲል 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ ወንድሞችና እህቶች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ እርስ በርስም ሆነ ለጎረቤቶቻቸው ተግባራዊና ስሜታዊ ድጋፍ ለመስጠት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው።
አብዛኞቹ ወንድሞችና እህቶች ከአገሪቱ ባይወጡም አንዳንዶች ግን ለመሸሽ ወስነዋል። ከሸሹት ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ ኬላዎችን ለማለፍ 30 ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት ለመሰለፍና ከሦስት እስከ አራት ቀን በዚያ ለመቆየት ተገድደዋል። በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ተሰልፈው እየጠበቁ ያሉትን ወንድሞቻቸውን ፈልገው በማግኘት ምግብና መጠጥን ጨምሮ የተለያየ እርዳታ አድርገውላቸዋል። ወንድሞችና እህቶች ድንበሩን ተሻግረው ወደ ጎረቤት አገሮች ሲገቡ ደግሞ በእነዚያ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች jw.org የሚል ምልክት ይዘው አቀባበል አድርገውላቸዋል፤ እነሱን ለማጽናናትና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ ሆነው ተቀብለዋቸዋል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
የሚያሳዝነው መጋቢት 1, 2022 በተከሰተው የቦንብ ፍንዳታ 1 መስማት የተሳነው ወንድም ሞቷል፣ ሚስቱ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባታል
3 ሌሎች እህቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል
ከ5,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው ሸሽተዋል
2 ቤቶች ወድመዋል
3 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
35 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
2 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል
ብዙ አስፋፊዎች የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የማሞቂያ መሣሪያና የስልክ አገልግሎት ችግር እንዲሁም የውኃ እጥረት አጋጥሟቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ ተቋቁመዋል
867 አስፋፊዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ቦታዎች ማረፊያ ማግኘት ችለዋል
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ እንደ ምግብና ውኃ ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ እየሠሩ ነው
ከላይ የሰፈሩት አኃዛዊ መረጃዎች መጀመሪያ ላይ የተሰበሰቡ ናቸው።
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አለመረጋጋት በነገሠበት በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ጥበብና ማስተዋል ተጠቅመው የወንድማማች ፍቅር ማሳየታቸውን መቀጠል እንዲችሉ እንጸልያለን።—ምሳሌ 9:10፤ 1 ተሰሎንቄ 4:9