ጥቅምት 25, 2023
ዩክሬን
በዩክሬን የተከናወነው ታሪካዊ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ከ30 ዓመት በኋላ ሲታወስ
ነሐሴ 7, 1993 በኪየቭ፣ ዩክሬን 7,402 ወንድሞችና እህቶች “መለኮታዊው ትምህርት” በተባለው ብሔራት አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተጠምቀው ነበር። ይህ ክንውን በዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው የተጠማቂዎች ቁጥር የተመዘገበበት ነው። በዕለቱ የተጠመቁ ሁሉ ይህ ልዩ ክስተት ፈጽሞ ከአእምሯቸው አይፋቅም።
በዚያን ቀን ከተጠመቁት መካከል ቮሎዲሚር እና ባለቤቱ አላ ይገኛሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ስብሰባ ላይ የተገኙትም በዚሁ ስብሰባ ላይ ነበር። በስብሰባው ላይ ከ16 አገራት የተውጣጡ 65,000 ሰዎች መገኘታቸውን በማስታወስ እንዲህ ይላሉ፦ “በኪየቭ የተደረገው ይህ ስብሰባ ዓለም አቀፉ ወንድማማች ማኅበር እንዲሁ በጽሑፎቻችን ላይ የምናነበው ነገር ሳይሆን በእርግጥ ያለ እውነታ መሆኑን አሳይቶናል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ባሉት ዓመታት ሁሉ በተገኘንባቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መንፈሳዊ ግቦችን በመከታተል ደስተኛ መሆን እንደሚቻል የሚመሠክሩ በርካታ ሕያው ምሳሌዎችን ማግኘት ችለናል።”
በኪየቭ የሚኖረው ወንድም ኦሌክሳንደር በዚያ ክልል ስብሰባ ላይ ከጉባኤው ከተጠመቁት 50 ወንድሞችና እህቶች አንዱ ነው። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “በቦታው የነበረውን ፍቅርና አንድነት ስመለከት ዓይኖቼ እንባ አቅርረው ነበር። አፍቃሪ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንዳለኝ እርግጠኛ ሆንኩ። እስከ አሁንም ድረስ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ ይህ ስሜት ይሰማኛል።”
እህት ሊዩድሚላ ስለ ጥምቀቷ ቀንና ስለ ስብሰባው ስታስታውስ እንዲህ ትላለች፦ “‘መለኮታዊው ትምህርት’ የተባለው ስብሰባ በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል። ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል ግብ አወጣሁ። ደግሞም ግቤ ላይ ደርሻለሁ፤ ላለፉት 28 ዓመታት ገደማ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስካፈል ቆይቻለሁ። ይሖዋ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ሲንከባከበኝ ቆይቷል።”
በእርግጥም በ1993 በኪየቭ የተደረገው “መለኮታዊው ትምህርት” የተባለው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የማይረሳ ክንውን ነው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በዩክሬን የአስፋፊዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ ገደማ ጨምሯል። ዛሬም ይሖዋ በዩክሬን ራሳቸውን በመወሰንና በመጠመቅ በድፍረት ከጎኑ የቆሙትን ሁሉ መባረኩን ቀጥሏል።—ዘፀአት 32:26