ሚያዝያ 27, 2022
ዩክሬን
በዩክሬን ያሉ ወንድሞች በድፍረት እርዳታ ያደርሳሉ እንዲሁም በጦርነት ቀጠና ያሉትን ይታደጋሉ
የካቲት 24, 2022 በዩክሬን ጦርነት ከተነሳ በኋላ አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት በሚታመሱ አካባቢዎች ውስጥ ይገኛሉ። የዩክሬን ከተሞች በሆኑት በክሬሜንቹክ እና በፖልታቫ የሚኖሩ 21 ወንድሞች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመታደግና የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማድረስ ሲሉ ወደ ጦርነት ቀጠናው ዘልቀው ለመግባት ፈቃደኛ በመሆን እውነተኛ የወንድማማች ፍቅር አሳይተዋል።
እነዚህ ወንድሞች እንደ ካርኪቭ ወዳሉ በጦርነት የሚታመሱ አካባቢዎች በስድስት ሳምንት ውስጥ 80 ጊዜ ገደማ በመመላለስ በድምሩ 50,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘው ወደ 400 የሚጠጉ ወንድሞችንና እህቶችን ታድገዋል።
እስካሁን ድረስ 23 ቶን ምግብ እንዲሁም መድኃኒት፣ ጋዝና ሌሎች ቁሳቁሶችን አድርሰዋል። ወንድሞች እያንዳንዱን ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት ጦርነት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች የራቀው መንገድ የቱ እንደሆነ በጥንቃቄ ያጠናሉ። ወንድሞች በየኬላው እየቆሙ መኪናቸው ስለሚፈተሽ አንዱ ጉዞ 19 ሰዓት ያህል ሊፈጅ ይችላል።
በሚጓዙበት ወቅት የጦር አውሮፕላኖች ከላያቸው ሲበሩ ይመለከታሉ። በተጨማሪም ወንድሞች በፈንጂ የፈራረሱ ሕንፃዎችን እንዲሁም ከጥቅም ውጪ የሆኑ ታንኮችንና መኪናዎችን ያያሉ። አንዳንድ ጊዜ ወንድሞች በአቅራቢያቸው ቦምብ ፈንድቶ መሬቱ ሲንቀጠቀጥ ይሰማቸዋል።
ሚያዝያ 2, 2022 ሮማን በካርኪቭ ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች የእርዳታ ቁሳቁስ ለማድረስ እየተዘጋጀ ሳለ በርካታ ሚሳኤሎች መሬት ላይ ሲወድቁ አየ። ከዚያም በአቅራቢያው በሚገኝ ሕንፃ ውስጥ ተሸሸገ። ከ30 ደቂቃ በኋላ ሲመለከት፣ ሊሄድበት የነበረው መንገድ በቦምብ ተደብድቦ አገኘ።
በመኪና እርዳታ ከሚያደርሱት ፈቃደኛ ሠራተኞች አንዱ የሆነው ቮሎዲሚር በአካባቢው ስላለው አደገኛ ሁኔታ ሲናገር “የጥበብ ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳን ወደ ይሖዋ አዘውትረን እንጸልያለን” ብሏል።
ኦሌክሳንደርና ባለቤቱ ቫለንቲና አረጋውያን ከሆኑት የኦሌክሳንደር ወላጆች ጋር በካርኪቭ ይኖሩ ነበር። በጦርነቱ ወቅት ከቤታቸው መስኮት 100 ሜትር ርቀት ላይ ቦምብ ሲፈነዳ ይመለከቱ ነበር። ሆኖም መኪና ስላልነበራቸው ከአካባቢው መሸሽ የሚችሉበት መንገድ አልነበረም።
ከዚያም ወንድሞች መጥተው ታደጓቸው። ኦሌክሳንደር “ስለረዱን ወንድሞች ለማመስገን ወደ ይሖዋ ጸለይን” ብሏል።
ቫሲል፣ ባለቤቱ ናታሊያ እንዲሁም ሦስት ልጆቻቸው ለበርካታ ቀናት ምድር ቤታቸው ውስጥ ተሸሽገው ነበር። ሆኖም የካቲት 29, 2022 በቤታቸው አቅራቢያ ቦምብ ፈነዳ። ፍንዳታው ቤታቸውን አፈራረሰው። ቫሲል፣ ፍንዳታው ጆሮ የሚያደነቁር ድምፅ እንዳሰማና የምድር ቤቱ መብራቶች በሙሉ እንደጠፉ ተናግሯል።
ውጊያው ጋብ ሲል ቤተሰቡ በአቅራቢያቸው ባለ ሕንፃ ወደሚገኝ ሌላ ምድር ቤት ሄዱ። መጋቢት 3, 2022 ወንድሞች አገኟቸው፤ እንዲሁም በአገሪቱ ወደሚገኝ ሰላማዊ ቦታ ወሰዷቸው።
ቫሲል ቤተሰቡ አካባቢውን ለቆ ወደ ሰላማዊ ቦታ ሲደርስ የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋን በጣም አመሰገንነው። ከረጅም ጊዜ በኋላ ስለ ልጆቻችን ደህንነት ሳንጨነቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰላም ራት በላን።”
ከሹፌሮቹ አንዱ የሆነው ኦሌክሳንደር፣ ወንድሞችን ለመታደግ የሚያደርጉት ጉዞ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምን ያህል እንደሚያስብ እንድመለከት ረድቶኛል። ወንድሞቻችን የሚያሳዩትን አመስጋኝነት ስመለከት ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል።”
እንዲህ ያሉ ደፋር ወንድሞች በማግኘታችን አመስጋኞች ነን፤ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በማሳየታቸው ይሖዋ እንዲባርካቸው እንጸልያለን።—ሮም 12:10