በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ናታሊያ (በስተ ግራ) እና ልጇ ሃብሪዬላ (በስተ ቀኝ) ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ኢኮኖሚያዊ ችግር ቢያጋጥማቸውም የተፈናቀሉ አስፋፊዎችን ቤታቸው አሳርፈዋል

ሐምሌ 20, 2022
ዩክሬን

እየተቸገሩም ሌሎችን መርዳት

እየተቸገሩም ሌሎችን መርዳት

በዩክሬን ባለው ጦርነት የተነሳ 47,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ብዙዎች በአገሪቱ ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ ወደማያጋልጡ አካባቢዎች የሸሹ ሲሆን በዚያ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውም ልብስ፣ ምግብ፣ መጠለያና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሰጥተዋቸዋል። እንግዳ ተቀባይ የሆኑት እነዚህ ወንድሞችና እህቶች እነሱ ራሳቸው ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያጋጠማቸው ቢሆንም የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው።

ኦልሃ (በስተ ቀኝ ጫፍ ላይ) ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር

በኡማን፣ ዩክሬን የምትኖረው ኦልሃ እና የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባለቤቷ፣ ጦርነቱ በተቆሰቆሰባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ 300 አስፋፊዎችን አስተናግደዋል። ተፈናቅለው ከመጡት ወንድሞችና እህቶች ብዙዎቹ እነኦልሃ ቤት ያደሩት አንድ ቀን ብቻ ነው፤ ከዚያ ጉዟቸውን ቀጥለዋል። አብዛኛውን ጊዜ ኦልሃ ወንድሞች እየመጡ መሆኑ የሚነገራት በውድቅት ሌሊት ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ በራቸው ይንኳኳል። ኦልሃ በአንድ ጊዜ 22 ወንድሞችንና እህቶችን ያስተናገደችበት ወቅት አለ። ይህ ሁኔታ የ18 ዓመቱ ልጇ ስታኒስላቭም ልግስና የማሳየት አጋጣሚ እንዲያገኝ መንገድ ከፍቷል። ስታኒስላቭ፣ የተፈናቀሉት ወንድሞች እሱ መኝታ ቤት ውስጥ እንዲያርፉ ሲል ብዙውን ጊዜ አልጋውን ለቆ መሬት ላይ ይተኛ ነበር።

ኦልሃ “በዚህ አደገኛ ወቅት የይሖዋን ሕዝብ መርዳት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ይህ ታላቅ መብት ነው” ብላለች።

ልዩድሚላ እና አንድሪ

አንድሪ እና ባለቤቱ ልዩድሚላ በአምስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ 200 ወንድሞችንና እህቶችን አስተናግደዋል። በአንድ ምሽት ብቻ 18 ሰዎችን የተቀበሉበት ጊዜም አለ። አንድሪ እንዲህ ብሏል፦ “ቅርንጫፍ ቢሮው የሰጠንን መመሪያ በመከተል የተወሰነ ምግብ ቤት ውስጥ አስቀምጠን ነበር። ይህም የተፈናቀሉትን ወንድሞች ለአሥር ቀን ያህል ለማስተናገድ አስቻለን። ወንድሞች ካርድ ውስጥ ገንዘብ አስቀምጠውልን ይሄዱ ነበር፤ እኛም በዚህ ተጠቅመን ለቀጣዮቹ እንግዶች እንዲሆነን ማግኘት የቻልነውን ምግብ እንገዛለን። የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴውም ምግብ ያመጣልን ነበር፤ ስለዚህ ምንም ነገር አጥተን አናውቅም።”

በኢቫኖ ፍራንኪቭስክ የምትኖረው ቪታ፣ በመጋቢት ወር አፓርትመንቷን ለተፈናቀሉ ወንድሞች ለቅቃ ከእህቷ ጋር መኖር ጀመረች። ቪታ እንዲህ ብላለች፦ “ፍቅሬን እንዳሳየሁ እንጂ መሥዋዕት እንዳደረግሁ አይሰማኝም። የተፈናቀሉትን ወንድሞች መርዳት መቻሌ ያስደስተኛል። ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን።”

ናታሊያ ከባለቤቷና ከሴት ልጇ ጋር በተርኖፒል ትኖራለች። ጦርነቱ ሲጀምር ሁሉም ከሥራቸው ተፈናቀሉ፤ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ቀደም ሲል ያጠራቀሙትን ገንዘብ መጠቀም ነበረባቸው። ያም ቢሆን አንዲት እህትንና የአካል ጉዳተኛ የሆነች ልጇን በእንግድነት ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ።

ቪታ (ከኋላ የቆመችው) አፓርትመንቷ ውስጥ ከሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር፤ እሷ ቤቷን ለቅቃ ከእህቷ ጋር እየኖረች ነው

ናታሊያ እንዲህ ብላለች፦ “አፍሪካ ውስጥ የምትኖር አንዲት እህት ተሞክሮ ትዝ አለኝ። ይህች እህት ያላት ቁሳዊ ነገር በጣም ትንሽ ቢሆንም ለክልል ስብሰባ የመጡ 14 ወንድሞችና እህቶችን ቤቷ አስተናግዳለች፤ ደግሞም ሁሉም የሚያስፈልጋቸው አግኝተዋል።” ናታሊያ ይህ ተሞክሮ የሌሎችን ፍላጎት እንድታስቀድም እንደረዳት ተናግራለች።

በዩክሬን የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢጋረጡባቸውም በይሖዋ በመታመን “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” አዳብረዋል።—ሮም 12:13