በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ኦሌና በቦምብ ፍንዳታ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ቤታቸው ፊት ለፊት። የእምነት ባልንጀሮቻቸው ወዲያውኑ ደርሰውላቸዋል

ሐምሌ 4, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 10 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

“ደፋር፣ አሳቢና እምነት የሚጣልባቸው”

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 10 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

በዩክሬን የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሁንም ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ያልተቋረጠ ድጋፍ እየሰጡ ነው። ራሳቸውን ሳይቆጥቡ አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ማሳየታቸውን ቀጥለዋል።

እህት ኦሌና 81 ዓመታቸው ነው። ሰኔ 6 ከቤታቸው በቅርብ ርቀት ላይ የጦር ሚሳይል ወደቀ። ሚሳይሉ የጎረቤታቸውን ቤት ያወደመው ሲሆን የወደቀበት ቦታ ላይ ሰባት ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ተፈጥሯል። ፍንዳታው በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ የእህት ኦሌና ቤት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

እህታችን እንዲህ ብለዋል፦ “ተኝቼ ነበር፤ በድንገት በራስጌዬ በኩል ያለው ግድግዳ ተደረመሰ። ጥቅጥቅ ያለ አቧራ አየሩን እፍን አደረገው። መስታወትና የድንጋይ ፍርስራሽ አካባቢውን ሞልቶታል። በሕይወት በመትረፌ ይሖዋ አመሰገንኩት።” ፍንዳታው በተሰማ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች ለእህት ኦሌና ደረሱላቸው፤ አንደኛው ወንድም በወቅቱ የራሱም ቤት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ነበር። እህት ኦሌና አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “ወንድሞች ቤቴ ሲደርሱ በጣም ከመደንገጣቸው የተነሳ ምን እንደሚሉ ግራ ገብቷቸው ነበር። ሆኖም መምጣታቸው በራሱ አጽናናኝ። ከጎኔ መሆናቸው በጣም አበረታታኝ።”

እህት ኦሌናን በጉባኤው ካሉ ወጣቶች ጋር ሆኖ አዘውትሮ የሚጠይቃቸው ሰርሂ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እህት ኦሌና ቤት አጠገብ ቦምብ እንደፈነዳ ስሰማ በጣም ደንግጬና ተጨንቄ ነበር። ትንሽ የተረጋጋሁት እህት ኦሌና፣ ሰውነታቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከመበለዙ ውጭ ከባድ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ስመለከት ነው። በጣም ያስገረመኝ፣ እህት ኦሌና ከአደጋው በኋላ ቤታቸው ውስጥ መጀመሪያ የፈለጉት ነገር ከጥቂት ቀናት በፊት የመጣላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ነበር።”

ደስ የሚለው ነገር ቤተሰቦቻቸው ሌላ ቤት አገኙላቸው። ጉባኤውም በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እየረዳቸው ነው፤ የጉባኤ ሽማግሌዎች እህት ኦሌናን በየቀኑ ይጠይቋቸዋል። እህታችን የጉባኤ ስብሰባዎችን ማዳመጥ እንዲችሉ ወንድሞችና እህቶች ለመስማት የሚረዳ መሣሪያ አመጡላቸው። እህት ኦሌና እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንድ ጊዜ ምንም አቅም እንደሌለኝ ይሰማኛል፤ ስብሰባዎች ግን በጣም ያበረቱኛል። የእምነት ባልንጀሮቼ አዘውትረው ይደውሉልኛል፤ ለሚያደርጉልኝ ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”

ከ200 አስፋፊዎች ጋር በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ምድር ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ አንድ ባልና ሚስት የነበሩበትን ሁኔታ ነግረውናል። ሚስትየው እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አፍቃሪ የሆኑት ሽማግሌዎች ያደረጉልን እንክብካቤ በጣም አስደንቆኛል። በጎቹን ከአንበሳና ከድብ ለማስጣል ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ይታገል የነበረውን ዳዊትን እንዳስታውስ አድርገውኛል። ምድር ቤት ውስጥ አብረውን የነበሩት የጉባኤ ሽማግሌዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ምግብና ውኃ እንዲሁም ለመብራት የምንጠቀምበት ጋዝ ያመጡልን ነበር። እነዚህ ወንድሞች ምስጋና ይግባቸውና የጉባኤ ስብሰባዎችንና የመስክ አገልግሎት ስብሰባዎችን ማድረግ ችለናል። ከባድ የቦምብ ድብደባ በነበረበት ጊዜም እንኳ እነዚህ ሽማግሌዎች፣ ወንድሞችንና እህቶችን ቤታቸው ድረስ እየሄዱ ይጠይቋቸው ብሎም ምግብና ውኃ ይወስዱላቸውና ያጽናኗቸው ነበር። ለእነዚህ ሽማግሌዎች ጥልቅ አክብሮት አለኝ። ይህ ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት እንደ አስተማሪዎችና ሰባኪዎች አድርጌ ነበር የማያቸው፤ አሁን ግን የምንተማመንባቸው እረኞችም እንደሆኑ ተገንዝቤያለሁ። ደፋር፣ አሳቢና እምነት የሚጣልባቸው በመሆናቸው የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል!”

በዩክሬን ያለ አንድ ጉባኤ አስፋፊዎች፣ የእርዳታ ሥራውን የሚያስተባብሩትን ወንድሞች በተመለከተ ለዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፈዋል፦ “ልባችን በጥልቅ አድናቆት ተሞልቷል። ይሖዋ በእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ያደረገልን እንክብካቤ በጣም አስደንቆናል። ኢየሱስ ‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ’ በማለት የተናገረው ሐሳብ በራሳችን ሕይወት ሲፈጸም ተመልክተናል።”—ዮሐንስ 13:35

እስከ ሰኔ 21, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 42 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 83 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 31,185 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  • 495 ቤቶች ወድመዋል

  • 557 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1,429 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 5 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል

  • 8 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 34 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 52,348 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 23,433 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው