በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዩክሬን ውስጥ ሁለት አስፋፊዎች በአደባባይ ምሥክርነት ሲካፈሉ

ሐምሌ 18, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 11 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

በጦርነት በምትታመስ አገር “መልካም ሥራ” መሥራት

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 11 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

በመላው ዩክሬን የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች፣ ሰዎችን በአካል አግኝተው መስበክ በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል፤ ግሩም ውጤቶችም እያገኙ ነው። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች ሪፖርት እንዳደረጉት ብዙዎች የጽሑፍ ጋሪያችንን እንደገና ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክሮችን ማየት ናፍቋቸው እንደነበረ ተናግረዋል።

በኦዴሳ ክልል ያለው የሰርሂቭካ ጉባኤ አስፋፊ የሆነችው ታቲያና ከወረርሽኙ በፊት ያገኘቻቸውን ሰዎች በአካል ሄዳ ለማነጋገር አሰበች። “አገልግሎታችንን እንደገና [በአካል ለማከናወን] የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እየባረከው መሆኑን ገና ከመጀመሪያው ነው ያየሁት” ብላለች። በአንድ ወቅት ታቲያና ከወረርሽኙ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ያልነበረች አንዲት ሴት ጋ ሄዳ ነበር። በዚህ ወቅት ሴትየዋ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ደስ እያላት የተወያየች ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣም ምንም ሳታመነታ ተቀበለች። ታቲያና “ቀደም ሲል ተመላልሶ መጠየቅ አደርግላቸው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ሄጄ ማነጋገርና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ መጋበዝ አለብኝ!” ብላለች።

ዬቨኒ እና ሊሊያ ከማሪዩፖል የተፈናቀሉ አስፋፊዎች ናቸው። በጦርነቱ ሳቢያ ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገድደዋል፤ በአሁኑ ወቅት ዩክሬን ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ በማያጋልጥ አካባቢ እየኖሩ ነው። ሁለቱም በስብከቱ ሥራ አዘውትረው ይካፈላሉ። አገልግሎት፣ ስላጋጠሟቸው ችግሮች እያሰቡ እንዳይቆዝሙ እንደረዳቸው ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወታችን መቼም ቢሆን እንደቀድሞው እንደማይሆን እናውቃለን። ኑሮን እንደ አዲስ ሀ ብሎ መጀመር በጣም ከባድ ነው፤ ሆኖም የይሖዋ እጅ አጭር እንዳልሆነ እናውቃለን። መንፈሱን ሰጥቶናል፤ በአዲሱ አካባቢ ያሉት ወንድሞቻችንም ደስ ብሏቸው እያገዙን ነው።”

በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወንድሞቻችን ደግሞ በመልካም ሥራቸውም ምሥክርነት እየሰጡ ነው። ለምሳሌ በሚኮላዬቭ ከተማ የሚገኙ የተወሰኑ ወንድሞች፣ ለእርዳታ ሥራ የሚያገለግል አንድ መጋዘንን በማደስና በማስተካከል ለአንድ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት እገዛ አበርክተዋል። ወንድሞች የውኃ መስመሮቹን አድሰዋል፣ መደርደሪያዎች አዘጋጅተዋል እንዲሁም በርከት ያሉ ቁሳቁሶችን በመልክ በመልክ አደራጅተዋል። የእርዳታ ድርጅቱ ተወካይ ሥራቸውን መጥታ በቃኘችበት ወቅት እንባ ተናንቋት ነበር። “ያከናወኑት ሥራ በጣም ነው ያስደነቀኝ” ብላለች።

በዩክሬን ያሉ ወንድሞቻችን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም በአገልግሎት በትጋት በመካፈልና “መልካም ሥራ” በመሥራት ደስተኛ መሆን ችለዋል።—ገላትያ 6:9

እስከ ሐምሌ 13, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 42 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 97 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 28,683 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  • 524 ቤቶች ወድመዋል

  • 588 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1,554 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 5 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል

  • 10 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 36 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 52,947 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 23,863 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው