በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 23, 2022 ዩክሬን ውስጥ የተጠመቁ ሁለት አስፋፊዎች

ነሐሴ 12, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 12 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

“ጦርነቱም ቢሆን ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ሊያስቆመው አልቻለም”

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 12 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ከሐምሌ 23 እስከ 31 ባሉት ቀናት፣ በመላው ዩክሬን የሚገኙና ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ሌሎች አገራት የሄዱ አስፋፊዎች “ሰላምን ተከተሉ!” በተባለው የ2022 የክልል ስብሰባ ላይ ተጠምቀዋል። እስከ ነሐሴ 2 ድረስ 1,113 የዩክሬን አስፋፊዎች ተጠምቀዋል። በዩክሬን ያለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ ‘ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ባለው መሠረት ጦርነቱም ቢሆን ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ሊያስቆመው አልቻለም።”—ማቴዎስ 28:20

አንዳንድ አስደሳች ተሞክሮዎችን እናካፍላችሁ፦

በክሬሚና፣ ሉሃንስክ ክልል የምትኖረው ናታሊያ 63 ዓመቷ ነው። እሷና ሁለት ሴቶች ልጆቿ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት የጀመሩት በ1990ዎቹ ነበር። ልጆቿ መንፈሳዊ እድገት አድርገው ተጠመቁ፤ እሷ ግን አልተጠመቀችም። ጦርነቱ ሲጀመር አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ናታሊያ አብራቸው እንድትሸሽ አደረጉ። ከዚያም በኢቫኖ ፍራንኪቭስክ በሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ መጠለያ ተሰጣት።

ናታሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ከቦምብ ድብደባው በኋላ ፈገግታ የሚባል ነገር ከፊቴ ላይ ጨርሶ ጠፍቶ ነበር። ወንድሞችና እህቶች እውነተኛ ፍቅር አሳዩኝ። እንዲህ ዓይነት እንክብካቤ አገኛለሁ ብዬ በፍጹም አልጠበቅሁም። ይህ ሁኔታ ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር እንዲቀሰቀስ አደረገ። መጽሐፍ ቅዱስን ሁልጊዜ አነብ ነበር፤ አንዲት እህት ደግሞ ለዘላለም በደስታ ኑር! በሚለው መጽሐፍ ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና ጠየቀችኝ። ከይሖዋ ያገኘኋት ስጦታ አድርጌ ነው የምቆጥራት።” ናታሊያ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “አሁን ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ በጣም ተደስቻለሁ። ከሁሉ የሚበልጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ይሖዋ አምላኬን ‘በሙሉ ልቤ፣ በሙሉ ነፍሴና በሙሉ አእምሮዬ መውደድ’ እፈልጋለሁ።”—ማቴዎስ 22:37

ፖላንድ ያለችው ኦልያ “ሰላምን ተከተሉ!” የተባለውን የክልል ስብሰባ ጭብጥ ይዛ

በቸርካሲ ትኖር የነበረችው ኦልያ ጦርነቱ ሲጀመር ያልተጠመቀች አስፋፊ ነበረች። መጋቢት 6 ከሴት ልጇና ከልጅ ልጇ ጋር ወደ ፖላንድ ሸሸች። እንዲህ ብላለች፦ “ፖላንድ ስንደርስ ከአደጋ ጊዜ ቦርሳችን በቀር ምንም አልያዝንም ነበር፤ ሆኖም መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶቻችን ሦስታችንንም ተንከባከቡን። ይህን ሁሉ ሳይ የይሖዋ ድርጅት አንድነት እንዳለውና በይሖዋ መንፈስ እንደሚመራ እርግጠኛ ሆንኩ። ያየሁት ነገር ሕይወቴን ለይሖዋ ለመወሰን ይበልጥ አነሳሳኝ። ይሖዋ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ረድቶኛል፤ ስለዚህ እሱን በማገልገል አመስጋኝነቴን ላሳየው እፈልጋለሁ።”

የ18 ዓመቷ ዩሊያ የምትኖረው በዶኔስክ ክልል ነው። ቤተሰቦቿ የይሖዋ ምሥክሮች ቢሆኑም እሷ ግን አልተጠመቀችም ነበር። ጦርነቱ ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ስላጋጠማቸው ሁኔታ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “መሬት ላይ ተኝቼ ነበር፤ በማንኛውም ቅጽበት ልሞት እንደምችል ታየኝ። የምንኖርበት ሰፈር እንዳለ ወደመ፤ የሚገርመው ቤተሰባችን ከጥቃቱ ተረፈ። በዚህ ሁኔታ ማለፌ እንዲሁም መጸለዬና በይሖዋ ባሕርያት ላይ ማሰላሰሌ ወደ እሱ ይበልጥ እንድቀርብ አደረገኝ፤ ‘ሕይወቴን ለይሖዋ ልወስን አልወስን’ እያልኩ ማመንታቴንም ተውኩ። ይሖዋ ጸሎቴን መመለሱ ምን ያህል እንደሚወደኝ አሳይቶኛል። በፊትም ቢሆን ስለ አምላክ አውቅ ነበር፤ አሁን ግን እወደዋለሁ።” ዩሊያ ሐምሌ 23 ተጠመቀች።

የ11 ዓመቱ ዴቪድ ጀርመን ውስጥ ከመጠመቁ በፊት

ጦርነቱ ሲፈነዳ የ11 ዓመቱ ዴቪድ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ጀርመን ሸሸ። ዴቪድ ከዘጠኝ ዓመቱ ጀምሮ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። አሁን መንፈሳዊ ግቦቹ ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረገ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ለመጠመቅ የወሰንኩት ይሖዋን ስለምወደውና የእሱ ጓደኛ መሆን ስለምፈልግ ነው። ስጠመቅ የይሖዋ አስደናቂ ቤተሰብ አባል በመሆኔ በደስታ አልቅሻለሁ። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው ለሰዎች መናገር ደስ ይለኛል፤ ስለዚህ ቀጣዩ ግቤ አቅኚ መሆን ነው። በጉባኤ ውስጥ ወንድሞቼንና እህቶቼን ማገልገልም እፈልጋለሁ፤ አንድ ቀን የጉባኤ አገልጋይ እንደምሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ትልቁ ግቤ ደግሞ ቤቴል መግባት ነው። በ2018 በልቪቭ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ ከጎበኘሁ ጀምሮ ሕልሜ እዚያ ገብቶ ማገልገል ነው።”

በኪየቭ ትኖር የነበረችው ኦሌና ያልተጠመቀች አስፋፊ የሆነችው በ2011 ነው። ሆኖም ለአሥር ዓመት ያህል ከጉባኤ ርቃ ነበር። በ2020 የጉባኤ ሽማግሌዎች አነጋገሯትና ወደ ይሖዋ ተመለስ የተባለውን ብሮሹር ሰጧት። እንዲህ ብላለች፦ “እንደገና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ሆኖም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በድጋሚ አቋረጥኩ። በጦርነቱ ወቅት ይሖዋ ጸሎቴን መለሰልኝ፤ ይሖዋ ጥበቃ እንዳደረገልኝ፣ ፍቅሩን እንዳሳየኝና ውስጣዊ ሰላም እንደሰጠኝ አስተዋልኩ። ወደ ሩማንያ ከሸሸሁ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። ወንድሞች ያደረጉልኝ እንክብካቤና ያሳዩኝ ፍቅር ይሖዋ የሚሞቅ ብርድ ልብስ እንዳለበሰኝ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።” ኦሌና ሐምሌ 24 ተጠመቀች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ይህን ያህል ስለታገሠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። አሁን ‘ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት እንዳለኝ’ ይሰማኛል።”—ፊልጵስዩስ 4:13

እስከ ነሐሴ 2, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 43 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 97 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 22,568 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  • 586 ቤቶች ወድመዋል

  • 613 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1,632 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 5 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል

  • 10 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 37 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 53,836 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 24,867 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው