በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 16, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 13 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

በአካል ወደሚደረገው አገልግሎት መመለስ

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 13 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ነሐሴ 2022 ዩክሬን ውስጥ የተሻለ ደህንነት ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነው አገልግሎት እንደሚጀመር ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደዚህ አገልግሎት ለመመለስ ጓጉተው ነበር። ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በደስታ እንደሚቀበሉ አስተውለዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፍላጎት ያሳየ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው በጦርነቱ ምክንያት የሚደርሰውን ሰቆቃና መከራ አይቶ ከአምላክ ውጭ መፍትሔ ይገኛል ብሎ እንደማያስብ ግልጽ ነው።” ከአገልግሎት የተገኙትን ተሞክሮዎች ከታች አቅርበንላችኋል።

በላኒቭጺ ጉባኤ የሚያገለግለው ሩስላን ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን አገልግሎት ዳግም ስለ መጀመር ሲያስብ ትንሽ ተጨንቆ ነበር። ከባለቤቱ ጋር ሆኖ ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጣቸው ጸለዩ፤ ብሩህ ተስፋ እየናፈቁ ካሉ ሰዎች ጋር እንዲያገናኛቸውም ይሖዋን ለመኑት። ባልና ሚስቱ አገልግሎት ከወጡ በኋላ የሚያስገርም ተሞክሮ ገጠማቸው፤ በሁለት ሰዓት ውስጥ ስምንት ሰዎችን አነጋገሩ፤ ስምንቱም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማሙ።

ኦልሃ የክሬሜኒትስ ጉባኤ አስፋፊ ነች፤ ከአንዲት እህት ጋር አገልግሎት ላይ ሳለች አንድ ሰው ወደ እነሱ እየሮጠ መጣ። ለሰዎች የአምላክን ቃል እያስተማሩ እንደሆነም ጠየቃቸው። ከዚያም እንዲህ ሲል ስለ ሁኔታው ነገራቸው፦ “አጨሳለሁ፤ የመጠጥ ችግርም አለብኝ። በቅርቡ በአምላክ ፊት ለፍርድ እንደምቆም አውቃለሁ። በዚያ ጊዜ አሁን ያለኝን ማንነት ይዤ መቅረብ አልፈልግም።” በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያሉ ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑት ዝግጅት ተደርጓል።

የለቪቭ-ርያስኔ-ስኪድኒ ጉባኤ አስፋፊ የሆነው ቫሲል ከአገልግሎት ቡድኑ ጋር ሆኖ በአንድ መንደር ውስጥ እያገለገለ ነበር፤ አንደኛው ቤት ከዓመታት በፊት ያናገራት አንዲት ሴት ቤት እንደሆነ ትዝ አለው። ሴትየዋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መነጋገር እንደማትፈልግ በቁጣ መልሳላቸው ነበር። ሆኖም በሩን አንኳኩቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ግብዣ ለማቅረብ ወሰነ። በሩን የከፈተችው ያቺው ሴት ናት፤ የሚገርመው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንደምትፈልግ ገለጸች። መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች፤ አንድ ሰው ተከታትሎ እንዲረዳት ዝግጅት ተደርጓል።

በኢሊንጺ ጉባኤ የሚያገለግለው ሴርሂ የተጠመቀው በ2021 ነው፤ ከቤት ወደ ቤት ሄዶ አገልግሎ አያውቅም። ፍርሃት ስላደረበት ብዙ ጊዜ ወስዶ ዝግጅት አደረገ። ሴርሂ እንዲህ ብሏል፦ “የውይይት ናሙና ቪዲዮዎቹን ደጋግሜ አየኋቸው። አንድ የቀረኝ ነገር ደፍሮ መውጣት ነበር።” ደስ የሚለው፣ ራሱን አደፋፍሮ አገልግሎት ወጣ፤ ለተለያዩ ሰዎች ምሥራቹን የመናገር አጋጣሚ በማግኘቱም ጭንቀቱ በደስታ ተተካ።

በሮስዲል ጉባኤ ያለችው ኒኮልም ያልተጠመቀ አስፋፊ የሆነችው ነሐሴ 2022 ነው። እንዲህ ብላለች፦ “በአካል አገልግሎት መውጣት በጣም አስጨንቆኝ እንዲያውም አስፈርቶኝ ነበር። አንዴ ከወጣሁ በኋላ ግን ሰዎችን በአካል አግኝቶ ስለ ይሖዋ መናገር በጣም አስደሳች እንደሆነ አይቻለሁ።”

ሁለት እህቶች ከቤት ወደ ቤት ሲሰብኩ

እስከ ኅዳር 11, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 46 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 97 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 12,569 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  • 590 ቤቶች ወድመዋል

  • 645 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1,722 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 6 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል

  • 19 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 63 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 53,948 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 25,983 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው