በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኃይል መቋረጥ፣ የዩክሬን ወንድሞቻችን ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ አላገዳቸውም። በስተ ግራ፦ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በአንድ ወንድም ቤት ውስጥ ለተሰበሰቡ ጥቂት አስፋፊዎች ንግግር እየሰጠ ነው። በስተ ቀኝ ከላይ፦ መብራት ባይኖርም በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ፕሮግራሙ አልተቋረጠም። በስተ ቀኝ ከታች፦ መብራት በተቋረጠበት ሰዓት አንድ ቤተሰብ በዙም አማካኝነት ስብሰባ ሲከታተል

ታኅሣሥ 20, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 14 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 14 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

በዩክሬን የተለያዩ አካባቢዎች በደረሰው ተደጋጋሚ ፍንዳታ፣ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል ወይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ወንድሞቻችን ኤሌክትሪክ የማያገኙበት ብዙ ጊዜ አለ፤ ያም ሆኖ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውንና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላቸውን አላቋረጡም።

መብራት በተቋረጠበት ሰዓት በዙም አማካኝነት ስብሰባ መከታተል

ኪየቭ ውስጥ በአቅኚነት የሚያገለግሉት አናስታሲያ እና ዲቦራ ሪፖርት እንዳደረጉት በቀን ቢያንስ ለ12 ሰዓት ያህል መብራት የላቸውም። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸውን መብራት እንደመጣ ቻርጅ ያደርጋሉ፤ ከዚያም የዳታ ኢንተርኔት ተጠቅመው ስብሰባ ይገባሉ። ስብሰባው ሲያበቃ ብዙውን ጊዜ ኢንተርኔት ይጠፋል።

የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ያስከተለው ሌላ ፈተና ደግሞ ከማሞቂያ ጋር የተያያዘ ነው። አንዳንድ ወንድሞች ለማሞቂያ የሚያስፈልጋቸውን ኤሌክትሪክ ለማግኘት ጄኔሬተር ያስነሳሉ። ሌሎች ወንድሞች፣ ማሞቂያ ያላቸው ዘመዶቻቸው ጋር ተጠግተዋል። ቅዝቃዜውን ከመቻል ውጪ አማራጭ የሌላቸውም አሉ። ደስ የሚለው፣ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ቤታቸው ያለው ማሞቂያ በጋዝ የሚሠራ ነው፤ ኤሌክትሪክ ቢጠፋም ማሞቂያውን መጠቀም ይችላሉ።

ኢቫኖ ፍራንክቪስክ ውስጥ በአቅኚነት የምታገለግለው ኢሪና አዎንታዊ ለመሆን ትጥራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከቁጥጥሬ ውጭ በሆነ ነገር ላይ ላለመጨነቅ ወስኛለሁ። የዕለቱን ብቻ ሳይሆን የሰዓቱን ነው የምኖረው። መብራት ሲጠፋ ማድረግ የምችለውን ነገር አቅዳለሁ፤ የሚያስፈልጉኝን ጽሑፎች አስቀድሜ አወርዳለሁ።”

የዩክሬን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩባቸውም ራሳቸውን በይሖዋ አገልግሎት አስጠምደዋል። ይሖዋ የሚያከናውኑትን “መልካም ሥራ” መባረኩን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—ገላትያ 6:9

እስከ ታኅሣሥ 6, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 47 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 97 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 11,537 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  • 590 ቤቶች ወድመዋል

  • 645 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1,722 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 7 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል

  • 19 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 68 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 54,212 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 26,811 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው