መጋቢት 16, 2022
ዩክሬን
ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 3 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል
በማሪዩፖል ከተማ በተከሰተ ፍንዳታ ሁለት እህቶቻችን መሞታቸውን ስንገልጽ በታላቅ ሐዘን ነው። በአሁኑ ወቅት ከባድ ጦርነት በመኖሩ ምክንያት ከተማዋን ለቀው መውጣት ያልቻሉ ከ2,000 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ባለፉት ጥቂት ቀናት 150 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከተማዋን ለቀው መውጣት ችለዋል። በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ የሚሠሩ ወንድሞች ወደ ማሪዩፖል የእርዳታ ቁሳቁስ ይዘው ለመግባት ቢሞክሩም የእነሱ መኪኖችም ሆኑ ሌሎች የእርዳታ መኪኖች ተኩስ ስለተከፈተባቸው ለመመለስ ተገደዋል። አንድ የጉባኤ ስብሰባ አዳራሽና አንድ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ባለበት ግቢ ውስጥ ፈንጂ ተጥሎ ነበር። በወቅቱ 200 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በስብሰባ አዳራሹ ምድር ቤት ውስጥ ተሸሽገው ነበር። ወንድሞቻችን ጉዳት ባይደርስባቸውም መኪኖቻቸው ወድመዋል፤ ይህም ከተማዋን ለቀው መውጣት ይበልጥ ከባድ እንዲሆንባቸው አድርጓል።
ከቤተሰቡ ጋር ማሪዩፖልን ለቆ መውጣት የቻለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ (ከታች በሥዕሉ ላይ የሚታየው) እንዲህ ብሏል፦ “ቤታችንን እና ሥራችንን አጥተናል፤ ከጓደኞቻችን ጋርም ተጠፋፍተናል። ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ አንድ ቀን የሚፈጀው ጉዞ ለእኛ ስድስት ቀን ወስዶብናል። በመኪና [ከከተማዋ ስንወጣ] መንገድ ላይ ገና ካልፈነዱ ፈንጂዎች የሚወጣ ጭስ ይታየን ነበር። በመንገዳችን ሁሉ ወንድሞቻችን ማረፊያና ምግብ እንድናገኝ ረድተውናል። የይሖዋን አባታዊ እንክብካቤ አይተናል። . . . ይህም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን እንዳለብን አሳምኖናል።”
ከዩክሬን የሸሹ የይሖዋ ምሥክር ስደተኞች ወደተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተጉዘዋል። ለምሳሌ አንድ የጉባኤ አገልጋይ፣ ባለቤቱ እንዲሁም የ7፣ የ11 እና የ16 ዓመት ልጆቻቸው ወደ ፖርቱጋል በመጓዝ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ዘመዶቻቸው ጋ ሄደዋል። ቤተሰቡ ድንበሩን ለማቋረጥ ለ11 ሰዓት ያህል ከጠበቁ በኋላ ለአራት ቀናት ከ4,000 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው የዘመዶቻቸው ቤት ደርሰዋል። የደረሱት ልክ የጉባኤ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ነበር። ቤተሰቡ ፖርቱጋልኛ ባይችሉም መንፈሳዊ ልማዳቸውን ይዘው ለመቀጠል በስብሰባው ላይ ተገኙ። ቤተሰቡ ብዙ ችግር ቢደርስባቸውም ደስተኛ በመሆናቸው የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች በጣም ተገረሙ።
ከቤተሰቧ ጋር ወደ ጀርመን የሸሸች አንዲት እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን፣ በአዎንታዊ ነገሮች ላይ ማተኮራችን እንዲሁም ወደፊት ስለሚጠብቀን ግሩም ተስፋ ማሰባችን በእጅጉ አበረታቶናል። . . . ይሖዋ በወንድሞቻችን አማካኝነት እንደረዳንና እንደመራን ተመልክተናል። ወንድሞቻችን በዩክሬን፣ በሃንጋሪ፣ አሁን ደግሞ በጀርመን ሞቅ አድርገው ተቀብለውናል፤ እንዲሁም በእጅጉ ረድተውናል!”
ይሖዋ በዩክሬን ያሉትን ውድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እየደገፋቸው እንዳለ በግልጽ ማየት ይቻላል።—መዝሙር 145:14
እስከ መጋቢት 7, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው በእጅጉ ሊበልጥ ይችላል፦
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
4 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል
19 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
29,789 አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው አገሪቱ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው ቦታዎች ሸሽተዋል
45 ቤቶች ወድመዋል
84 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
366 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
16 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው
20,981 አስፋፊዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ቦታዎች ማረፊያ ማግኘት ችለዋል
11,973 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው