በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ ዩክሬን ውስጥ በአንድ ምድር ቤት የተሸሸጉ እህቶች። በስተ ቀኝ፦ ወንድሞቻችን በዩክሬን የእርዳታ ቁሳቁሶችን ሲያደራጁ

መጋቢት 23, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 4 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 4 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

በማሪዩፖል ጦርነቱ እና ፍንዳታው አሁንም አላቆመም፤ በመሆኑም በዚያ ስላሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አጥብቀን መጸለያችንን እንቀጥላለን። የሚያሳዝነው፣ በፍንዳታው ምክንያት ስድስት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሞተዋል። ዩክሬን ውስጥ በድምሩ አሥር ወንድሞችና እህቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተጨማሪም በዜና ዘገባዎች ላይ እንደወጣው፣ ባለፈው ሳምንት ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች በተጠለሉበት ቲያትር ቤት ውስጥ ፈንጂ ፈንድቶ ነበር። በዚህ ጥቃት የሞተ የይሖዋ ምሥክር ባይኖርም ጥቂት ወንድሞችና እህቶች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

እስካሁን 750 ገደማ ወንድሞቻችን ከማሪዩፖል ሸሽተው ወጥተዋል፤ 1,600 ገደማ የሚሆኑት ግን አሁንም እዚያው ናቸው። ብዙዎቹ የሚገኙት አሁን በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው በከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል ነው።

ከዚህ በፊት ዜና ላይ እንደወጣው፣ 200 ገደማ ወንድሞችና እህቶች የስብሰባ አዳራሽና የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በሚገኝበት ሕንፃ ምድር ቤት ውስጥ ተሸሽገው ነበር። እዚያ ከነበሩት ወንድሞች ጋር ለአጭር ጊዜ መገናኘት በቻልንበት ወቅት ወንድሞች የሚከተለውን መረጃ ሰጥተውናል፦

“በፍንዳታው ወቅት አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በጣም ፈርተው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ማልቀስ ጀመሩ። ውጭ ያለውን ፍንዳታ ስንሰማ፣ ወይ በፍንዳታው ወይም በእሳቱ ምክንያት ልንሞት እንደምንችል አስበን ነበር። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የመንግሥቱን መዝሙሮች እንድንዘምር ሐሳብ አቀረበ። በተከታታይ ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ መዝሙሮችን ዘመርን። የፍንዳታው ድምፅና የሕንፃው መንቀጥቀጥ ይበልጥ በጨመረ ቁጥር፣ እኛም ድምፃችንን ይበልጥ ከፍ አድርገን እንዘምር ነበር። ከዚያም መዝሙር 27⁠ን አንብበን ተወያየንበት። በኋላም ሁሉም ወንድሞች የሚወዷቸውን ጥቅሶችና እነዚያ ጥቅሶች ያበረታቷቸው እንዴት እንደሆነ ተናገሩ። . . . በእርግጥም ይሖዋ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜም ጭምር ሊያረጋጋን የሚችል ‘የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ እንደሆነ ተመልክተናል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመፈለግና አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ምግብና መድኃኒት ለማድረስ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ወንድሞች ከተማው ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ተባራሪ ጥይት እንዳይመታቸው መሬት ላይ እየተንፏቀቁ መሄድ ይጠበቅባቸዋል። ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ሲሉ ‘ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡትን’ ወንድሞቻችንን በጣም እንኮራባቸዋለን።—ሮም 16:4

በከተማው ውስጥ ነዳጅና ኤሌክትሪክ ስለሌለ ደፋር የሆኑ እህቶች ደጅ እሳት አንድደው ምግብ ያበስላሉ። ከዚያም ምግቡ በዕድሜ ለገፉና የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ አስፋፊዎች ይወሰድላቸዋል። ብዙዎቹ ወንድሞቻችን ቤታቸውን፣ መኪናቸውንና ንብረታቸው አጥተዋል፤ ሆኖም የእምነት ባልንጀሮቻቸው ለሚያሳዩአቸው ፍቅርና እንክብካቤ አመስጋኝ ናቸው።

እህቶች ከተሸሸጉበት ምድር ቤት በር አቅራቢያ ደጅ ላይ ምግብ ሲያበስሉ

በተለያዩ ቦታዎች ተሸሽገው ያሉት ክርስቲያኖች አብረው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች በማካፈል በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላቸውን ለመቀጠል ጥረት እያደረጉ ነው።

እስከ መጋቢት 22, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 10 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 27 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 33,180 አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው አገሪቱ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው ቦታዎች ሸሽተዋል

  • 78 ቤቶች ወድመዋል

  • 102 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 484 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1 የስብሰባ አዳራሽ ወድሟል

  • 4 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 18 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 25,069 አስፋፊዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ቦታዎች ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 14,308 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው