ሚያዝያ 1, 2022
ዩክሬን
ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 5 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል
በጣም የሚያሳዝነው፣ እስከ መጋቢት 29, 2022 ድረስ በማሪዩፖል ከተማ የሚኖሩ ሌሎች ሰባት ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በሞት ተነጥቀናል። በድምሩ ዩክሬን ውስጥ 17 ወንድሞችና እህቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ዩክሬን ውስጥ ያሉ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ ለማድረስ ሲሉ በትጋት እየሠሩ ነው፤ እንዲያውም በጦርነት በሚታመሱ አካባቢዎች ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማግኘት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል።
ለአብነት ያህል፣ በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞች በጦርነቱ ከባድ ጉዳት በደረሰባቸው ከተሞች ለምሳሌ በካርቪቭ፣ በክራምቶርስክና በማሪዩፖል ምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን እያደረሱ ነው። አንድ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል 2,700 ለሚሆኑ አስፋፊዎች እርዳታ ለማድረስ በርካታ የጦር ሠራዊቱን ኬላዎች እያለፈ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት በየቀኑ ይጓዛል።
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ወንድሞችንና እህቶችን ከጦርነት ቀጠና ለማስወጣት መጓጓዣም ያዘጋጃሉ። በቸርንሂቭ ባለ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግል አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ወታደሮቹ መኖሪያ ቤቶችን በቦምብ መደብደብ ሲጀምሩ ከተማው ውስጥ መቆየት በጣም አደገኛ እንደሆነ ተረዳን። የኤሌክትሪክና የኢንተርኔት አገልግሎት ስለተቋረጠ በቦምብ ድብደባው ወቅት ሽማግሌዎች ከተማዋ ውስጥ በየምድር ቤቶች ወደተሸሸጉት አስፋፊዎች ሄደው ከከተማዋ ለመውጣት የመጓጓዣ ዝግጅት እንደተደረገ ነገሯቸው።”
የአንድ የመጓጓዣ ድርጅት ባለቤት ሚኒባሶቹንና አውቶቡሶቹን ለማቅረብ ተስማማ፤ 254 ወንድሞችንና እህቶችን ከቸርንሂቭ ከተማ ለማስወጣት ዘጠኝ ጊዜ ተመላልሷል። እንዲያውም አንዴ አውቶቡሱን ለማሳለፍ ሲል መንገዱን በከባድ ማሽን መጠገን ነበረበት። ወንድሞቻችን እንዲህ ያለ እርዳታ በማግኘታቸው አመስጋኝነታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ጦርነት ቤተሰቦቻቸውን ካጡ ጋር አብረን እናዝናለን። የአምላክ ቃል በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተሰጠን ተስፋ መሠረት ሞት እና ሐዘን የማይኖርበትን ጊዜ ሁላችንም በጉጉት እንጠባበቃለን።—ራእይ 21:3, 4
እስከ መጋቢት 29, 2022 ድረስ የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
17 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል
35 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
36,313 አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው ቦታዎች ሸሽተዋል
114 ቤቶች ወድመዋል
144 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
612 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
1 የስብሰባ አዳራሽ ወድሟል
7 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
23 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው
34,739 አስፋፊዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል
16,175 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው