በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ በዩክሬን ያሉ ወንድሞችና እህቶች ከፖላንድ የመጡ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ መኪና ሲጭኑ። በስተ ቀኝ፦ በሆስቶሜል የሚገኝ በቦምብ የወደመ የአንድ ወንድም ቤት

ሚያዝያ 13, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 6 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 6 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

የሚያሳዝነው፣ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ተጨማሪ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን አጥተናል። እስካሁን 28 የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በዓለም አቀፋዊ የዜና አውታሮች ላይ እንደተዘገበው በኪየቭ አቅራቢያ የሚገኙ ከተሞች በተለይ ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያ ሳምንታት ከባድ ውጊያ ላይ ነበሩ። በዚያ አካባቢ ከሚኖሩት 4,900 ገደማ አስፋፊዎች መካከል ከ3,500 በላይ የሚሆኑት ሰላማዊ ወደሆኑ አካባቢዎች ሸሽተዋል።

የሚከተሉት ተሞክሮዎች በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ወንድሞቻችን እጅግ በጣም ከባድ ፈተና ቢደርስባቸውም የማይናወጥ እምነት እያሳዩ ያሉት እንዴት እንደሆነ ያሳያሉ።

በማካሪቭ ከተማ የሚኖር ኦሌክሳንደር የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ በማዕከላዊ ዩክሬን ወደሚገኝ ሰላማዊ ቦታ ሸሸ። ሆኖም በመስክ አገልግሎት ቡድኑ ያሉ አራት አስፋፊዎችን ማግኘት ስላቃተው እነሱን ለመፈለግ ወደ ጦርነት ቀጠናው ተመለሰ። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ አገልጋዮቹን በጣም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ተገንዝቤ ነበር። . . . ወደ አንደኛው አስፋፊ ቤት ስደርስ ግቢው ውስጥ ቦምብ እንደፈነዳ ተመለከትኩ። የምድር ቤቱ በር ተዘግቶ ነበር፤ ብጣራም የሚመልስልኝ ሰው አላገኘሁም። በዚህ ጊዜ ፈራሁ።” ኦሌክሳንደር የምድር ቤቱን በር ሰብሮ ሲገባ እዚያ የነበሩት ሰዎች ሁሉ አፈጠጡበት። አስፋፊዎቹንና አብረዋቸው የተሸሸጉትን የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ጎረቤቶቻቸውን አገኘ።

ያሮስላቭና ባለቤቱ (መሃል) እንዲሁም ኦሌክሳንደርና ባለቤቱ ወደ ሰላማዊ ቦታ ከደረሱ በኋላ አብረው ሲመገቡ

በምድር ቤቱ ውስጥ ከነበሩት አስፋፊዎች አንዱ የሆነው ያሮስላቭ እንደገለጸው በምድር ቤቱ ውስጥ ለስምንት ቀናት ተሸሽገው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዳችን በቀን የምንበላው ጥቂት ብስኩቶች ከአንድ ብርጭቆ ውኃ ጋር ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስና ጽሑፎቻችንን እናነብ፣ እንጸልይ እንዲሁም እርስ በርስ እንበረታታ ነበር። ኦሌክሳንደር ስሜን ሲጠራ ወታደሮቹ ሊወስዱኝ የመጡ መስሎኝ ነበር። መሞቴ ነው ብዬ አሰብኩ። . . . ኦሌክሳንደር ግን የሁላችንንም ሕይወት አተረፈልን። ይሖዋ የሚጸልዩልን አልፎ ተርፎም እኛን ለመታደግ ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሰዎችን ያቀፈ አፍቃሪ መንፈሳዊ ቤተሰብ ስለሰጠን በጣም እናመሰግነዋለን።”

ፒሊፕ

ፒሊፕ እና አንድ ሌላ ወንድም በቦሮዲያንካ ከተማ ለቀሩ አስፋፊዎች ምግብ ለመውሰድ አሰቡ። መጋቢት 17 ወደ ከተማይቱ በመኪና እየሄዱ ሳሉ ወታደሮች አስቆሟቸውና የያዙትን ምግብ ወሰዱት። ከዚያም ወታደሮቹ ሁለቱንም ወንድሞች በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው፤ እጃቸውን በካቴና አስረውና ዓይናቸውን ሸፍነው ምድር ቤት ውስጥ ወዳለ ትንሽ ክፍል ወሰዷቸው፤ በዚያም ሌሎች ሰባት ወንዶች ነበሩ። ከሁለት ቀን በኋላ ወደ እስር ቤት የተወሰዱ ሲሆን ምሽት ላይ ጠባቂዎቹ ይደበድቧቸው ነበር። ፒሊፕ “በሕይወት መትረፌን ተጠራጥሬ ነበር። ታማኝ ለመሆን እንዲረዳኝ ጸለይኩ” ብሏል።

በአንድ ወቅት እየተደበደቡ ሳሉ ፒሊፕ፣ ምግብ ማግኘት ስላልቻሉት አረጋዊ እህቶችና ስለ ቤተሰቡ ደህንነት ጮክ ብሎ መጸለይ ጀመረ፤ በተጨማሪም ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት በደስታ ማገልገል በመቻሉ አመሰገነው። ጠባቂው ወደሚታሰርበት ክፍል ከመለሰው በኋላም ወታደሮቹ ወንድሞች አደገኛ ሰዎች አለመሆናቸውን እንዲገነዘቡ መጸለዩን ቀጠለ። ሁለቱም ወንድሞች ለጠባቂዎቹ መመሥከር ጀመሩ። ለሁለት ቀናት በየፈረቃው ለሚገቡት ጠባቂዎች መሠከሩላቸው። በተጨማሪም ከእስረኞቹ መካከል አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ሆነ። ወንድሞችን አመሰገናቸው። መጋቢት 27 ወንድሞችና ፍላጎት ያሳየው ሰው ከእስር ተለቀቁ።

በቡቻ የምትኖር ስቪትላና የምትባል ያላገባች እህት ለሁለት ሳምንታት ከጦርነት ቀጠናው መሸሽ አልቻለችም ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የሚሰጠው ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተገንዝቤያለሁ። የአምላክ ሰላም አለን ሲባል የችግሮቻችን መፍትሔ ሁልጊዜ ይታየናል ማለት አይደለም። ሆኖም መውጫ ቀዳዳ ሲጠፋን በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንታመናለን ማለት ነው።”

ስቪትላና ሰላማዊ ወደሆነ የዩክሬን ክፍል እየተጓዘች ሳለ ለአንዲት ሴትና ለዘመዷ መሠከረችላቸው። ሁሉም ሰላማዊ ወደሆነ ቦታ ሲደርሱ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ተቀበላቸው። ቤተሰቡ ስቪትላናን እንዲሁም ሴትየዋንና ዘመዷን አሳረፏቸው። በቀጣዩ ቀን፣ ሴትየዋ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስና ጽሑፎቻችንን ለመውሰድ ጠየቀች። ስቪትላና ሴትየዋን ማነጋገሯን ቀጥላለች።

እስከ ሚያዝያ 12, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 28 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 48 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 40,778 አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው ቦታዎች ሸሽተዋል

  • 278 ቤቶች ወድመዋል

  • 268 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 746 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1 የስብሰባ አዳራሽ ወድሟል

  • 9 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 26 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 41,974 አስፋፊዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ቦታዎች ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 18,097 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው