በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በልቪቭ 60 ገደማ ወንድሞችና እህቶች በተጠለሉበት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የመታሰቢያው በዓል ሲከበር

ሚያዝያ 29, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 7 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ከ210,000 በላይ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኙ

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 7 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ይሖዋ በዩክሬን የሚኖሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንደባረካቸውና በመላዋ አገሪቱ ያሉ ወንድሞቻችን የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ማክበር እንደቻሉ ስንገልጽላችሁ በጣም ደስ ይለናል። በምዕራባዊ ዩክሬን ባሉ ወንድሞቻችን በተጠለሉባቸው በርካታ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ የመታሰቢያው በዓል ተከብሯል። ወንድሞቻችን የመታሰቢያውን በዓል በዋነኝነት ያከበሩት በትናንሽ ቡድኖች ሆነው ነው፤ ከቤታቸው መውጣት ያልቻሉ አስፋፊዎች ደግሞ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባውን ተከታትለዋል።

ካርቪቭ ውስጥ ወንድሞችና እህቶች የመታሰቢያውን በዓል ምድር ቤት ውስጥ ሲያከብሩ

በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በመታሰቢያው ዕለት ቀኑን ሙሉ የማስጠንቀቂያ ደወል ሲጮኽ ነበር። ምሽት ላይ ግን ድምፁ ጠፋ። በድሩዢክቫ፣ ዶንቴስክ የሚኖረው ሼሪ እንዲህ ብሏል፦ “የመታሰቢያው በዓል በፍንዳታ ምክንያት እንዳይቋረጥ ስንጸልይ ነበር። ልክ በዓሉ ሊጀምር ሲል ፍንዳታውም አቆመ፤ የማስጠንቀቂያ ደወሉም አቆመ።”

በኪየቭ አቅራቢያ በኔሚስሄቭ የነበሩ አረጋውያንና አቅመ ደካማ አስፋፊዎች ለአንድ ወር ያህል በስብሰባዎች ላይ መገኘት አልቻሉም። በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት ሲጸልዩ ነበር። ቪታሊ የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የመታሰቢያውን በዓል አብሯቸው አከበረ። እንዲህ ብሏል፦ “ኤሌክትሪክ የለም፤ ስለዚህ በዓሉን ያከበርነው በእጅ ባትሪ ነው። አየር ማሞቂያውም አይሠራም። ሙዚቃ አልነበረም፤ ስለዚህ ልጄ ቫዮሊን እየተጫወተች መዝሙራችንን አጀበችልን።”

በጦርነት ቀጠናው ውስጥ የሚኖር ኦሌክሳንደር የተባለ ሽማግሌ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በመታሰቢያው በዓል ዘመቻ ወቅት በጉባኤያችን ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች ደብዳቤ መጻፍ አልቻልንም ነበር፤ ምክንያቱም ቤቶቹ በቦምብ ስለተደበደቡ የሚኖርባቸው የለም። በመሆኑም የምናውቃቸውን ሌሎች ሰዎች ለምሳሌ ምድር ቤት አብረውን የተደበቁ ሰዎችን እንዲሁም ከመኖሪያቸው አብረውን የሸሹ ሰዎችን መጋበዝ ጀመርን። ብዙዎቹ ሰዎች ከዚህ ቀደም የይሖዋ ምሥክሮች ሲመሠክሩላቸው ሰምተው አያውቁም። ብዙ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ አብረውን ተገኝተዋል።”

በዩክሬን የሚኖሩ ባልና ሚስት የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ የመታሰቢያውን በዓል በሻማ ሲያከብሩ። ስልካቸውን በአቅራቢያው ባለ መንደር በጀነሬተር ቻርጅ አስደርገዋል

ዩክሬን ውስጥ ካሉት ጉባኤዎች በሙሉ አጠቃላይ ሪፖርት እስካሁን ባይደርሰንም ከ210,000 በላይ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንደተገኙ ታውቋል።

በዩክሬን የሚኖር አንድ ወንድማችን ስለ መታሰቢያው በዓል ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የወደብ መብራት መርከበኞች ዳርቻው ላይ መድረሳቸውን እንደሚያረጋግጥላቸው ሁሉ የመታሰቢያው በዓል የይሖዋ ቀን ቅርብ እንደሆነ አረጋግጦልኛል። የዘንድሮ የመታሰቢያ በዓል ደግሞ ይህን ስሜቴን ይበልጥ አጠናክሮታል።”

እስከ ሚያዝያ 21, 2022 ድረስ የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 35 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 60 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 43,792 አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው ቦታዎች ሸሽተዋል

  • 374 ቤቶች ወድመዋል

  • 347 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 874 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1 የስብሰባ አዳራሽ ወድሟል

  • 10 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 27 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 44,971 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 19,961 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው