ግንቦት 23, 2022
ዩክሬን
ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 8 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል
ጦርነቱ እየቀጠለ ሲሄድ ለወንድሞች የሚደረገው እረኝነትም ተጧጡፏል
በዩክሬን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ በሄደበት በዚህ ወቅት የዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ በአገሪቱ ለሚገኙ ወንድሞች እረኝነት ለማድረግ እየተጋ ነው። በመላው አገሪቱ የሚገኙ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አስፋፊዎች እረኝነት ለማድረግ ብዙ እየደከሙ ነው። የእረኝነት ጉብኝቱ ወንድሞችን እያበረታታ ነው። አንድ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል በምዕራብ ዩክሬን የሚገኙ የተፈናቀሉ ወንድሞችንና እህቶችን ጎብኝቶ ነበር፤ በኡዥጎሮድ ከተማ በሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከ30 ወንድሞችና እህቶች ጋር ተጠልላ የምትገኝ አንዲት እህት አድናቆቷን ስትገልጽ “ይሖዋ እጆቹን ዘርግቶ ያቀፈኝ ያህል ነው የተሰማኝ” ብላለች።
ወንድሞች፣ በ27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ውስጥ ለሚያገለግሉ 100 ገደማ ወንድሞችም በትጋት እረኝነት እያደረጉ ነው። ኢሆር የተባለ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል እንዲህ ሲል ሐሳቡን አጋርቶናል፦ “በእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ እንዳገለግል የተመደብኩት እኔና ባለቤቴ ከመኖሪያችን ተፈናቅለን ሰው ጋር ተጠልለን ባለንበት ወቅት ነው። በጣም ዝለን በነበረበት ወቅት ለራሱ በጣም ሥራ የሚበዛበት አንድ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሊጠይቀን መጣ፤ ደግሞም በጥሞና አዳመጠን። ስለ ደህንነታችን ከልብ ማሰቡ ነክቶናል።” ኢሆር አክሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ የይሖዋን እጅ የምናየው እንደ ጨቅላ ሕፃን ምንም ማድረግ እንደማንችል በሚሰማን ወቅት ነው፤ ምንም መውጫ መንገድ ስናጣ ያለን አማራጭ ወደ ይሖዋ መጸለይ ብቻ ይሆናል፤ ያኔ የይሖዋ እጅ በግልጽ ይታየናል።”
በጦርነት ቀጠና ውስጥ ካሉ የስብሰባ አዳራሾቻችን ጋር በተያያዘ 4ቱ ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ፣ 8ቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ 33ቱ ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሪፖርት ደርሶናል።
እስከ ግንቦት 17, 2022 ድረስ የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
37 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል
74 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
45,253 አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው ቦታዎች ሸሽተዋል
418 ቤቶች ወድመዋል
466 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
1,213 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
4 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል
8 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
33 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው
48,806 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል
21,786 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው