በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድሞችና እህቶች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ሲያጓጉዙ

ሰኔ 10, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 9 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ወቅታዊ መረጃ ቁጥር 9 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

የዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ በ27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እየታገዘ በአገሪቱ ለሚገኙ የተፈናቀሉ ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ማድረጉን ቀጥሏል። ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ምግብ፣ ልብስና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ከ250 ቶን በላይ የእርዳታ ቁሳቁስ ከፖላንድ ወደ ዩክሬን ገብቷል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም ባለባቸው የዩክሬን ግዛቶች የሚኖሩ ወንድሞችም ከ80 ቶን በላይ የምግብ እርዳታ ልከዋል።

በኪየቭ የምትኖር ቫለንቲና የተባለች እህት በእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞች ስላደረጉላት ድጋፍ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ውጊያው ሲጀምር ከተማው ውስጥ መቆየት በጣም አደገኛ ነበር። ስለዚህ በቸርካሲ ክልል ወደምትገኝ ትንሽ ከተማ ሸሸሁ። እዚህ ከመጣሁ ሁለት ወር አልፎኛል። በአካባቢው ባለው ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በጣም እንደሚያስቡልኝ አሳይተዋል። በርከት ያለ ምግብና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ አምጥተውልኛል። ያደረጉልኝን እርዳታ ስመለከት ልቤ በጥልቅ ተነካ። አንደኛው እሽግ ውስጥ ብላንካ የተባለች የአራት ዓመት ልጅ የሣለችውን ሥዕልና ፖስት ካርድ አገኘሁ። . . . ሥዕሉንና ካርዱን ማስታወሻ እንዲሆነኝ አስቀምጠዋለሁ። ወንድሞቼና እህቶቼ ላሳዩኝ ደግነት ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንኩ በቃላት መግለጽ ይከብደኛል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋን አመሰግናለሁ!”

ልጆችም በእርዳታ ቁሳቁሶቹ ውስጥ የሚካተቱ ሥዕሎችን በመሣል የበኩላቸውን እያደረጉ ነው

የአካል ጉዳተኛ የሆኑና በሲዬቬሮዶኔስክ የሚኖሩ ቫለንቲና የተባሉ ሌላ የ83 ዓመት እህትም እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ጦርነቱ ሲጀምር የምኖረው ብቻዬን ነበር። ያለኝ አንድ ልጅ ከጦርነቱ በፊት ሞቶብኛል። ከተማዋ ሙሉ ቀን በቦምብ ስትደበደብ ስለምትውል ሁኔታው እጅግ በጣም አስፈሪ ነበር። ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልም ሆነ ጋዝ አልነበረም፤ የኢንተርኔት አገልግሎቱም ደካማ ነበር። ወንድሞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ስለረዱኝ በጣም አመሰግናለሁ።”

አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “በኋላ ላይ ወንድሞች እኔንና የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሁለት እህቶችን አንጻራዊ ሰላም ወዳለበት ወደ ኒፕሮ ከተማ ወሰዱን። በኒፕሮ ከተማ ያሉ ወንድሞች ማረፊያ አዘጋጁልኝ። አሁን የምኖረው ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ጋር ነው፤ እነሱም እንደ ቤተሰባቸው አድርገው ይንከባከቡኛል። በስብሰባዎች ላይ መገኘትና መሳተፍ እንድችል ዘመናዊ ስልክ ሰጥተውኛል። ወንድሞች ያሳዩኝን ደግነት መቼም ቢሆን አልረሳውም።”

አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ በዩክሬን ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንድም “መልካም ነገር [እንዳይጎድልባቸው]” እየተንከባከባቸው ነው፤ ይህን በማየታችን ልባችን በደስታና በአመስጋኝነት ተሞልቷል።—መዝሙር 34:10

እስከ ሰኔ 7, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 42 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 82 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 46,145 አስፋፊዎች ቤታቸውን ጥለው ሸሽተዋል

  • 469 ቤቶች ወድመዋል

  • 540 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1,405 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 5 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል

  • 8 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 33 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 50,663 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እርዳታ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 22,995 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው