መጋቢት 11, 2022
ዩክሬን
ወቅታዊ መረጃ | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል
እንደ ማሪዩፖል ባሉ ጦርነቱ የተፋፋመባቸው አካባቢዎች ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጧል፤ የቤት ማሞቂያ አይሠራም፤ እንዲሁም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት አልተቻለም። ብዙ ቤቶች መስኮታቸው ተሰባብሯል። የምግብና የውኃ አቅርቦት እጥረት አጋጥሟል። ከ2,500 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ከማሪዩፖል መውጣት አልቻሉም። በአንዳንድ ከተሞች (ለምሳሌ በቡቻ፣ በቼርኒሂቭ፣ በሆስቶሜል፣ በኢርፒን፣ በኪየቭ እና በሰሚ) ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ የሚያስችሉ መተላለፊያ መንገዶች ተከፍተው ነበር። በመሆኑም በርካታ ወንድሞች የተሻለ ደህንነት ወዳለባቸው ቦታዎች መሸሽ ችለዋል።
በሆስቶሜል የሚኖር የ36 ዓመት የጉባኤ ሽማግሌና አቅኚ ከሚስቱና ከወላጆቹ ጋር ሸሽቷል። በከተማው ውስጥ ጦርነቱ ሲካሄድ የነበረውን ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦
“ሄሊኮፕተሮች ከቤታችን በላይ ይበርሩ ነበር። የወታደር መኪኖች በየመንገዱ አይጠፉም። ምድር ቤት ተደብቀን ሳለ ወታደሮች ሰብረው ገብተው ነበር። ከወታደሮቹ አንዱ ወደ ምድር ቤቱ አከታትሎ ተኮሰ። የእናቴ ቦርሳ በጥይት ቢመታም ከእኛ መካከል የተጎዳ ሰው አልነበረም። በወቅቱ ለሦስት ወይም ለአራት ሰዓት ያህል በቤታችን ዙሪያ የቦምብ ፍንዳታና የተኩስ ልውውጥ ነበር፤ እኛ ግን ድምፅ ሳናሰማና ምንም እንቅስቃሴ ሳናደርግ እዚያው ምድር ቤት ውስጥ ቆየን። . . . በነጋታው ጠዋት በመኪና እየሸሸን ሳለ በአቅራቢያችን ጦርነት ተጀመረ። መንገዱ ላይ ታንኮች ነበሩ። . . . ሁኔታው በጣም አደገኛ ነበር፤ እዚያ ብንቆይ ደግሞ የባሰ አደጋ ላይ እንወድቅ ነበር።
“እነዚህ ሁኔታዎች ሕይወታችንን በእጅጉ ቀይረውታል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተምረናል። ለምሳሌ ስለ ነገ አለመጨነቅን፣ ባሉን መሠረታዊ ነገሮች መርካትን እንዲሁም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነንም በይሖዋ መታመንን ተምረናል።”
አምላካችን ይሖዋ በዩክሬን የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በደንብ እንደሚረዳ እናውቃለን። እሱ ፈጽሞ አይተዋቸውም።—2 ጴጥሮስ 2:9
እስከ መጋቢት 10, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል፦
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
2 አስፋፊዎች ሞተዋል
8 አስፋፊዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል
25,407 አስፋፊዎች ቤታቸውን ትተው በአገሪቱ ውስጥ ወዳሉ አንጻራዊ ደህንነት ያለባቸው ቦታዎች ሸሽተዋል
25 ቤቶች ወድመዋል
59 ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል
222 ቤቶች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል
7 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
27 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው
10,566 አስፋፊዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ቦታዎች ማረፊያ ማግኘት ችለዋል
9,635 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው