በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኪየቭ ክልል በቬሊካ ዲሜርካ ጉዳት የደረሰበት አንድ ቤት ከጥገና በፊትና በኋላ

ታኅሣሥ 29, 2022
ዩክሬን

ወቅታዊ መረጃ 15 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

ወቅታዊ መረጃ 15 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል

የካቲት 2022 ከተቀሰቀሰው የዩክሬን ጦርነት ወዲህ 3,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ወድመዋል። ወንድሞች በአደጋ ጊዜ እርዳታ እና በአካባቢ ንድፍና ግንባታ የሥራ ክፍሎች አስተባባሪነት ነሐሴ ወር ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች መጠገን ጀምረዋል፤ እርግጥ ይህ ሥራ የተጀመረው አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ነው። የጥገና ሥራው የተጎዱ ጣሪያዎችን ማደስ፣ የተሰበሩ መስኮቶችን መተካትና ሌሎች አነስተኛ ጥገናዎችን ያካትታል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ከወደመ መኪና ማቆሚያውን በማስተካከል አነስ ያለ ቤት ለመሥራት ጥረት ተደርጓል። እስካሁን ድረስ 37 የግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዋል፤ 48 ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው።

በዚህ ነውጠኛ ጊዜ የግንባታ ሥራ ማከናወን ቀላል አይደለም። ሆኖም ወንድሞች በእርዳታ ሥራ ከመካፈል ወደኋላ አላሉም። በኪየቭ ክልል የቬሊካ ዲሜርካ ነዋሪ የሆነችው የ70 ዓመቷ እህት ስቬትላና እንዲህ ብላለች፦ “የቤቴን ጣሪያና የፊት ለፊቱን ክፍል ለማደስ ገንዘብ አልነበረኝም። ይሖዋ ያልጠበቅኩትን ነገር አድርጎልኛል። ወንድሞቼ መጥተው በሦስት ቀን ውስጥ ሁሉን ነገር አስተካክለውልኛል።”

በኪየቭ ክልል የሆሬንካ ነዋሪ የሆነችው እህት ናዲያ፣ የእርዳታ ሥራው ለስብከቱ ሥራም ድጋፍ እንደሆነ ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “የጥገና ሥራው ለሁሉም ሰው ምሥክርነት ሰጥቷል። የማላውቃቸው ሰዎችም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያሳዩት እውነተኛ ፍቅር ሲናገሩ ሰምቻለሁ። የእምነት አጋሮቼ ለእኔ ብለው ይህን ሁሉ ማድረጋቸው በጣም አስገርሟቸዋል።”

የራሳቸውን ቤት ያጡ ወንድሞችና እህቶችም እንኳ በሥራው እያገዙ ነው። ለምሳሌ ዬቭሄን እና ቴትያና የተባሉ ባልና ሚስት ቤታቸው በሚሳይል ተመቶ ወድሞባቸዋል። ሆኖም ባጡት ነገር ላይ ከመቆዘም ይልቅ የእምነት አጋሮቻቸውን ለመርዳት ተግተው እየሠሩ ነው። ዬቭሄን እንዲህ ብሏል፦ “ዋናው ፍላጎታችን ሌሎችን መርዳት ነው። ሰዎችን ስንረዳ የራሳችንን ችግር ለመቋቋም አቅም እናገኛለን።”

አንጻራዊ ሰላም አለ ተብሎ በሚታሰብባቸው ቦታዎች የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ቤቶች ሲጠግኑ

በኪየቭ ክልል የምትኖረው ሊዲያም በሆስቶሜል የሚገኘውን ቤቷን ወንድሞች ጠግነውላታል፤ ይህም በእርዳታ ሥራ እንድትካፈል አነሳስቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ለሁለት ሳምንታት 16 ወንድሞችና እህቶች ቤቴን ለመጠገን ደፋ ቀና ሲሉ ነበር። አዲሱ ዓለም የገባሁ ያህል ነው የተሰማኝ። አሁን እኔም ሌሎች የመርዳት ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኛል።”

የዩክሬን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነ አንድ ወንድም የእርዳታ ሥራ የሚከናወንባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት ቤታቸውን ላጡ ወንድሞችና እህቶች ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የዩክሬን ወንድሞች ድሮም በፍቅራቸው የታወቁ ናቸው። ይህ ጦርነት ግን ይበልጥ አቀራርቧቸዋል። እነዚህ ውድ ወንድሞቻችን የተደረገላቸው እርዳታ በአገልግሎት ተጨማሪ ነገር እንዲያደርጉ እንዲሁም 2 ቆሮንቶስ 9:12 እንደሚለው ‘ለአምላክ ብዙ ምስጋና እንዲያቀርቡ’ ሲያነሳሳቸው ማየት የሚያበረታታ ነው።”

እስከ ታኅሣሥ 20, 2022 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  • 47 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል

  • 97 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 11,477 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  • 590 ቤቶች ወድመዋል

  • 645 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1,722 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 7 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል

  • 19 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 68 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • 26 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው

  • 54,212 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል

  • 26,892 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው