የካቲት 1, 2023
ዩክሬን
ወቅታዊ መረጃ 16 | በዩክሬን ቀውስ ቢከሰትም የወንድማማች ፍቅር ታይቷል
የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ዳግመኛ ጀመረ
ዩክሬን ውስጥ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የዘወትር አቅኚዎችና ልዩ አቅኚዎች ከታኅሣሥ 26, 2022 አንስቶ በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ መማር ጀምረዋል። እንደ አካባቢው ሁኔታ አቅኚዎቹ በአካል ወይም በዙም ትምህርቱን ይከታተላሉ። የአየር ድብደባ፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ እንዲሁም ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ፤ ያም ቢሆን ወንድሞችና እህቶች ይህ ልዩ የትምህርት ፕሮግራም እንዳያመልጣቸው የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። በውጤቱም ብዙ መንፈሳዊ በረከቶች አግኝተዋል።
ናታሊያ ከክሪቪ ሪህ እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ቤቱ ልክ እንደ ሕይወት አድን መንሳፈፊያ ሆኖልኛል። በጭንቀትና በፍርሃት እንዳልሰምጥ ረድቶኛል።” አናስታሲያም ከቸርኒቭትሲ እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ቤቱ፣ ይሖዋ በጣም እንደሚወደኝ አሳምኖኛል። ያለፈው ዓመት ብዙ ውጥንቅጥ ያየንበት ነበር፤ ይህ ትምህርት ቤት ልክ በሚያስፈልገኝ ወቅት ላይ ነው የመጣው። የይሖዋን በረከት ለማግኘት በማደርገው ተጋድሎ እንድገፋበት አነሳስቶኛል።”
በኪትስማን አቅኚ ሆና የምታገለግለው ስቪትላና ትምህርት ቤቱን እንድትካፈል ግብዣ ሲቀርብላት መጀመሪያ ላይ ሁኔታው አስጨንቋት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ያለብኝን የኢኮኖሚ ችግር ጨምሮ የሚያስጨንቀኝን ነገር ሁሉ ለይሖዋ ነገርኩት። በእሱ ታመንኩ፤ ይህን በማድረጌም አልተቆጨሁም። የይሖዋን ፍቅርና እንክብካቤ ቀምሻለሁ።” የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው የስቪትላና ባለቤት የእሷን ጥረት ሲመለከት አብሯት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ።
በዢቶሚር ትምህርት ላይ የነበሩ አቅኚዎች የአየር ድብደባ ማስጠንቀቂያ ደወል ስለተሰማ ሁለት ጊዜ ምድር ቤት ለመጠለል ተገድደው ነበር። የእንጨት ምድጃ ለኩሰው ክፍሉን በማሞቅ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በቅርቡ ኑሮዋን በዢቶሚር ያደረገችው ቫለንቲና እነዚህ ከባድ ሁኔታዎች እያሉም ስለተሰማት ነገር ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ትምህርት ቤት ፈጽሞ አልረሳውም። በይሖዋ ኃያል ክንዶች ሥር የተጠለልኩ ያህል ሆኖ ነው የተሰማኝ።”
በሌሎች በርካታ አገሮች እንደሆነው ሁሉ የዩክሬን አቅኚዎችም የሚጠበቅባቸው ሰዓት መቀነሱን ሲሰሙ በጣም ተደስተዋል። ማስታወቂያውን ከሰማች በኋላ ዩሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ልቤ ለይሖዋ ባለኝ ፍቅር ተሞልቷል። ይሖዋን በዚህ አገልግሎት እንድጸና እንዲረዳኝ የለመንኩት ዛሬ ጠዋት ነው። እንዴት መልስ እንደሚሰጠኝ ባላውቅም እንደሚመልስልኝ እርግጠኛ ነበርኩ። የሚጠበቅብን ሰዓት እንደተቀነሰ ስሰማ ይሖዋ ላደረገልኝ ነገር ያለኝ አድናቆት እጅግ ጨምሯል። በትምህርት ቤቱ መጨረሻ ላይ የሰማነው ይህ ዜና ከምግብ በኋላ እንደሚቀርብ ጣፋጭ ነገር ሆኖልኛል።”
እስከ ጥር 24, 2023 ድረስ ከዩክሬን የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር መረጃ መለዋወጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ትክክለኛው ቁጥር እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
47 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል
97 አስፋፊዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
8,953 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
590 ቤቶች ወድመዋል
645 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
1,722 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
8 የስብሰባ አዳራሾች ወድመዋል
17 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
76 የስብሰባ አዳራሾች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
26 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዩክሬን ውስጥ በሥራ ላይ ናቸው
46 ቤቶች ታድሰዋል
5 የስብሰባ አዳራሾች ታድሰዋል
54,445 ሰዎች በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እገዛ፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ማግኘት ችለዋል
27,655 አስፋፊዎች ወደ ሌሎች አገሮች ሸሽተዋል፤ በዚያም የእምነት አጋሮቻቸው እርዳታ እያደረጉላቸው ነው