በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኦሌክሳንደር ትሬትየክ

ታኅሣሥ 28, 2020
ዩክሬን

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በእምነቱ ምክንያት ለተደበደበው ለወንድም ኦሌክሳንደር ትሬትየክ ፈርዶለታል

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በእምነቱ ምክንያት ለተደበደበው ለወንድም ኦሌክሳንደር ትሬትየክ ፈርዶለታል

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የከሳሽ ትሬትየክ እና የተከሳሽ ዩክሬን መንግሥትን ጉዳይ ከተመለከተ በኋላ ታኅሣሥ 17, 2020 ወንድም ኦሌክሳንደር ትሬትየክን የሚደግፍ ብይን አስተላልፏል። ወንድም ትሬትየክ ኅዳር 26, 2013 ከአገልግሎት ወደ ቤቱ እየተመለሰ ሳለ ሦስት ሰዎች ክፉኛ ደበደቡት። የዩክሬን ባለሥልጣናት የተፈጸመውን ወንጀል ለማጣራት ተገቢውን እርምጃ እንዳልወሰዱ ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ፣ ወንድም ኦሌክሳንደር ትሬትየክ 7,500 ዩሮ (9,100 የአሜሪካ ዶላር) ካሳ እንዲከፈለው ወስኗል።

ወንድም ትሬትየክ የደረሰበት ድብደባ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ወደ አንድ ወር ገደማ ሆስፒታል መተኛት አስፈልጎታል። ፖሊስ ግን ወንጀሉን ማጣራት የጀመረው ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሦስት ወር በኋላ ነው። ፖሊሶቹ፣ ጥቃቱ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ወንጀል ነው ማለት አልፈለጉም፤ እንዲሁም ወንድም ትሬትየክ የደረሰበት ጉዳት ከባድ መሆኑን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም። በኋላ ላይም፣ ፖሊስ ክሱን በቀላል ወንጀል ምድብ ፈርጆታል። በተጨማሪም ጥቃቱን ከፈጸሙት ሦስት ሰዎች መካከል ጥፋተኛ ነው የተባለው አንዱ ብቻ ነው፤ ያውም ይህ ውሳኔ የተላለፈው ግለሰቡ ከአገር ሸሽቶ ከወጣ በኋላ ነው። የቀሩት ሁለቱ የጥቃቱ ፈጻሚዎች (አንደኛው ፖሊስ ነው) የቀረቡት ምሥክሮች ሆነው ነው። በዚህ ወንጀል ማንም የተቀጣ ሰው የለም። ወንድም ትሬትየክ በ2015 ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ጉዳዩን ያቀረበው በእነዚህና በሌሎች መንገዶች ግልጽ የፍትሕ ጥሰት ስለነበረ ነው።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ “[የዩክሬን] ባለሥልጣናት በተበዳይ ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማጣራት ተገቢውን እርምጃ እንዳልወሰዱ” ገልጿል፤ ይህ ደግሞ ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ጋር የሚጻረር ነው።

ይህ ውሳኔ፣ በዩክሬንም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ሃይማኖታዊ መብት ያስከብራል የሚል እምነት አለን። ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ፍትሕ እንድናገኝ የረዳን ይሖዋ ነው።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:59