በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 20, 2020
ዩክሬን

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በዩክሬን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፉ ውሳኔዎችን አስተላለፈ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በዩክሬን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፉ ውሳኔዎችን አስተላለፈ

ፍርድ ቤቱ፣ በወንድሞቻችን ላይ ባላቸው ሃይማኖታዊ ጥላቻ ተነሳስተው ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦችን እየቀጣች ባለመሆኑ ዩክሬንን አወገዘ

ኅዳር 12, 2020 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በዩክሬን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፉ ሦስት ውሳኔዎችን አስተላለፈ። ውሳኔዎቹ የተላለፉት ዛጉብኒያ እና ታባችኮቫ፣ ሚጎርያኑ እና ሌሎች እንዲሁም ኮርኒሎቫ በዩክሬን ላይ ከመሠረቷቸው ክሶች ጋር በተያያዘ ነው። ክሶቹ ለፍርድ ቤቱ የቀረቡት በ2014 እና በ2015 ነው። እያንዳንዱ ክስ የተመሠረተው የሕግ አስፈጻሚ አካላት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሰዎችን ባለመቅጣታቸው ነው። የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤቱ የዩክሬን ባለሥልጣናት የወንድሞቻችንን መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዳላስጠበቁ በመግለጽ ለተጎጂዎቹ የ14,700 ዩሮ (17,400 የአሜሪካ ዶላር) ካሳ እንዲከፈል አዟል።

ዛጉብኒያ እና ታባችኮቫ በዩክሬን ላይ የመሠረቱት ክስ፦ ሚያዝያ 20, 2009 እህት ዛጉብኒያ እና እህት ታባችኮቫ፣ ኖቪ ምሊኒ በተባለች መንደር ውስጥ ከቤት ወደ ቤት እየሰበኩ ነበር። በአካባቢው ያለ የሥላሴ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ የሆነው ሚኮል ሊሴንኮ እህቶችን መንገድ ላይ ሲያገኛቸው ጭንቅላታቸውንና ጀርባቸውን በዱላ በኃይል ደበደባቸው። ቄሱ እህቶቻችንን “ማስፈራራት” እንዲሁም “እንቅስቃሴያቸውን ማስቆም” ፈልጎ እንዳደረገው በገዛ አንደበቱ ቢናገርም ለፈጸመው ድርጊት ምንም ዓይነት ቅጣት አልተላለፈበትም።

ሚጎርያኑ እና ሌሎች በዩክሬን ላይ የመሠረቱት ክስ፦ ሚያዝያ 5, 2012 ሃያ አንድ የይሖዋ ምሥክሮችና የተወሰኑ እንግዶች የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ተሰብስበው ሳለ የሞስኮ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ በሆነ ግሬኩ የተባለ ሰው የተመራ የረብሸኞች ቡድን ስብሰባውን አቋርጦ ገባ። ከዚያም ረብሸኞቹ ጸያፍ ንግግር መናገር እንዲሁም ልጆችንና በዕድሜ የገፉ ሴቶችን ጨምሮ ተሰብሳቢዎቹን ማስፈራራት ጀመሩ።

ይህ ቄስ እና ተባባሪዎቹ በሌሎች አጋጣሚዎችም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የቀጠሉ ሲሆን ከፈጸሟቸው ጥቃቶች መካከል ወንድሞችን መደብደብ፣ የአንድን ወንድም መኪና ማቃጠልና የይሖዋ ምሥክሮቹ ተኝተው ወዳሉበት ክፍል ቦምብ (ቤት ውስጥ የተሠራ) መወርወር ይገኙበታል። ተጎጂዎቹ እነዚህ የጥቃት ድርጊቶች ከተፈጸሙባቸው በኋላ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት ያደረጉ ከመሆኑም ሌላ ለባለሥልጣናቱ ማስረጃ አቀረቡ። ሰዎቹ ጥቃቱን ሲፈጽሙ የሚያሳዩ አንዳንድ ቪዲዮዎችም ተገኝተዋል። ሆኖም ፖሊስ እነዚህን ጥቃቶች በሃይማኖታዊ ጥላቻ ምክንያት እንደተፈጸሙ ወንጀሎች አድርጎ ለመቁጠር ፈቃደኛ አልሆነም፤ በተጨማሪም በቪዲዮዎቹ ላይ ጥቃት የፈጸሙትን ሰዎች መለየት እንደማይቻል ገልጿል። ቄሱም ሆነ ተባባሪዎቹ ለፈጸሙት ድርጊት ምንም ዓይነት ቅጣት አልተላለፈባቸውም።

ኮርኒሎቫ በዩክሬን ላይ የመሠረተችው ክስ፦ መጋቢት 7, 2013 ኖሲቭካ በተባለች ከተማ ውስጥ እህት ኮርኒሎቫ እና እህት ሴርዲዩክ ጎረቤቶቻቸውን በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንዲገኙ እየጋበዙ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ አንድ ሰው ጸያፍ ንግግር መናገርና ሃይማኖታቸውን ማንቋሸሽ ጀመረ። ከዚያም እህት ኮርኒሎቫን ፊቷ ላይ በኃይል የመታት ሲሆን ጭንቅላቷ ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰባት። በዚህም ምክንያት ለ11 ቀን ያህል ሆስፒታል ውስጥ ተኛች። ፖሊስ እህታችን ጥቃት የተፈጸመባት “በግል ጥላቻ” የተነሳ እንጂ በሃይማኖታዊ ጥላቻ ምክንያት እንዳልሆነ ተናግሯል። ፍርድ ቤቱ ጥቃቱን በፈጸመው ግለሰብ ላይ ቀላል ቅጣት ጥሎበታል።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ እህት ቴቲያና ኮርኒሎቫ፣ እህት ቴቲያና ዛጉብኒያ፣ እህት ማሪያ ታባችኮቫ እና ወንድም ቫሲል ሚጎርያኑ። ከ2009 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ በሃይማኖታዊ ጥላቻ ምክንያት ጥቃት ከተፈጸመባቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አራቱ

የዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለሚደርሰው ስደት ለመነጋገር ከአካባቢው፣ ከአገሪቱና ከዓለም አቀፍ ባለሥልጣናት ጋር በተደጋጋሚ ስብሰባ አድርገው ነበር። ወንድሞች ያሏቸውን አማራጮች በሙሉ ከተጠቀሙ በኋላ በ2014 ጉዳዩን ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ማቅረብ ጀመሩ። የሚገርመው፣ ይህ ከመሆኑ ከአንድ ዓመት በፊት ባለሥልጣናቱ በዩክሬን እየታየ ያለውን ሃይማኖታዊ ጥላቻ ማስተዋል ጀምረው ነበር። የዩክሬን እንባ ጠባቂ ተቋም በ2013 ያቀረበው ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ሃይማኖታዊ ጥላቻን ሊጠቁሙ የሚችሉ ወንጀሎች በደንብ ምርመራ የማይደረግባቸው መሆኑ ጥቃቱን የሚፈጽሙት ሰዎች በድርጊታቸው እንዲገፉበት ያበረታታል።” በተመሳሳይም የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ በ2013 ባቀረበው ሪፖርት ላይ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚፈጸመውን ጨምሮ በጥላቻ ምክንያት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ዩክሬን ውስጥ እንደ ቀላል ወንጀል የሚታዩ መሆኑ እንዳሳሰበው ገልጿል። ኮሚቴው ሪፖርቱን ሲደመድም፣ የዩክሬን መንግሥት “በጥላቻ ምክንያት የሚፈጸሙ ወንጀሎች በደንብ ምርመራ እንዲደረግባቸው፣ ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ . . . እንዲሁም ወንጀለኛ ሆነው ከተገኙ ተገቢው ቅጣት እንዲተላለፍባቸውና ተጎጂዎቹ በቂ ካሳ እንዲሰጣቸው ለማድረግ የበለጠ ጠንክሮ መሥራት” እንዳለበት አሳስቧል።

ባለፉት ዓመታት የዩክሬን መንግሥት ሁኔታውን ለማሻሻል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል። በአገሪቱ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ነፃነት ያላቸው ቢሆንም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፋቸው እነዚህ ሦስት ውሳኔዎች በዩክሬንም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ የሕግ አስፈጻሚ አካላት የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ሃይማኖታዊ ነፃነት ማስጠበቃቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚያነሳሷቸው እንተማመናለን። “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ” የሆኑት ይሖዋ በአገልጋዮቹ ላይ የሚደርሰውን ስደት ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን።—ዘዳግም 32:4