በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 31, 2019
ዩክሬን

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ በዩክሬን የስብሰባ አዳራሽ እንዲገነባ መንገድ ከፈተ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ በዩክሬን የስብሰባ አዳራሽ እንዲገነባ መንገድ ከፈተ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት መስከረም 3, 2019 ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ በዩክሬን፣ ክሪቪይ ሪህ ከተማ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ። የክሪቪይ ሪህ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ለመገንባት የሚያስፈልጋቸውን ፈቃድ ሆን ብሎ በመከልከሉ ጥፋተኛ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ወንድሞች በክሪቪይ ሪህ፣ ዩክሬን አዳራሽ ለመገንባት ከገዙት ቤት ፊት ለፊት ቆመው

ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ማዘጋጃ ቤቱ ሁለት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ጥሷል፤ እነሱም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 9 (የሐሳብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት) እንዲሁም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ምዕራፍ 1 አንቀጽ 1 (የንብረት ባለቤት የመሆን መብት) ናቸው። በመሆኑም ማዘጋጃ ቤቱ አዳራሹ የሚገነባበት መሬት ባለንብረት ለሆኑት ሁለት ጉባኤዎች የ7,000 ዩሮ ካሳ መክፈል አለበት። የዩክሬን መንግሥት በሦስት ወራት ውስጥ ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ጠቅላይ ችሎት ይግባኝ መጠየቅ ይችላል።

በክሪቪይ ሪህ የሚገኙት ሁለቱ ጉባኤዎች የስብሰባ አዳራሽ ለመገንባት ማመልከቻ ካስገቡ ከ15 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። ጉባኤዎቹ ነሐሴ 9, 2004 በከተማው ይዞታ ሥር ያለ አንድ የመኖሪያ ቤት ከገዙ በኋላ የአምስት ዓመት ሊዝና አዳራሽ የመገንባት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ማመልከቻ አስገቡ። ማዘጋጃ ቤቱ መስከረም 28, 2005 የመጀመሪያውን ፈቃድ ሰጠ። ከዚያም ጉባኤዎቹ ግንባታ ለመጀመር የሚያስችለውን የመጨረሻውን ፈቃድ ማግኘት የሚችሉት ንድፋቸውን ለአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ካሳዩ በኋላ እንደሆነ ተነገራቸው።

ወንድሞች ንድፉን አዘጋጅተው ለሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ካሳዩ በኋላ የመጨረሻውን ፈቃድ ለማግኘት ነሐሴ 23, 2006 ለማዘጋጃ ቤቱ ማመልከቻ አስገቡ። ማዘጋጃ ቤቱ በአንድ ወር ውስጥ ውሳኔውን የማሳወቅ ሕጋዊ ግዴታ ቢኖርበትም ለማመልከቻው ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል። የክልሉ ፍርድ ቤት የማዘጋጃ ቤቱ ድርጊት ሕገ ወጥ እንደሆነ የሚገልጽ ውሳኔ ቢያስተላልፍም ማዘጋጃ ቤቱ የመጨረሻውን ፈቃድ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ወንድሞች በአገሪቱ ባሉ ሌሎች ፍርድ ቤቶች አማካኝነት መፍትሔ ለማግኘት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀረ፤ በዚህም ምክንያት ሚያዝያ 13, 2010 ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በክሪቪይ ሪህ ለሚገኙ ወንድሞቻችን በመፍረዱ ደስተኞች ነን። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአምልኮ ስፍራ መገንባት አስቸጋሪ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችን የስብሰባ አዳራሽ መገንባት እንዲችሉ ይረዳቸው ዘንድ እንጸልያለን።—መዝሙር 118:5-9