በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 12, 2019
ዩክሬን

የዩክሬን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስብሰባ አዳራሻችን የመጠቀም መብታችንን አስከበረ

የዩክሬን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስብሰባ አዳራሻችን የመጠቀም መብታችንን አስከበረ

በተትዬቭ፣ ዩክሬን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለአራት ዓመት ፍርድ ቤት ከተከራከሩ በኋላ የስብሰባ አዳራሻቸውን ለአምልኮ እንዲጠቀሙበት ተፈቀደላቸው። ወንድሞቻችን አዳራሹን ገንብተው የጨረሱት ታኅሣሥ 2014 ነበር፤ ሆኖም የክልሉ የሥነ ሕንፃ ምክር ቤት አዳራሹን ለመጠቀም የተጠየቀውን ፈቃድ ስድስት ጊዜ ውድቅ በማድረግ፣ ጉባኤውን ከፍተኛ መቀጮ በማስከፈል እንዲሁም ሕንፃው ተገንብቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም የግንባታ ፈቃዱን በመሰረዝ ሕንፃው ጥቅም ላይ እንዳይውል ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞክሯል።

ጥቅምት 10, 2018 የዩክሬን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንድሞቻችን የግንባታ ሕጎችን እንዳከበሩ ገልጿል። በተጨማሪም የአውሮፓ አገራት የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት የአምልኮ ቦታ የመገንባት መብትን እንደሚደግፍ ፍርድ ቤቱ ገልጿል። አዲስ የተሾመው የክልሉ የሥነ ሕንፃ ምክር ቤት ኃላፊ ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን ፈቃድ መጋቢት 28, 2019 ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ጉባኤው በዚያው ወር የመጀመሪያውን ስብሰባ ማካሄድ ችሏል።

ኅዳር 2, 2019 ወንድሞች፣ የአካባቢው ሰዎች የስብሰባ አዳራሹን እንዲጎበኙ ዝግጅት አድርገው ነበር። በዚህም የተነሳ የከተማውና የወረዳው ባለሥልጣናት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች አዳራሹን ጎብኝተዋል። የተትዬቭ ክልል አስተዳደር ዋነኛ የሥነ ሕንፃ ባለሙያ የሆኑት አናቶሊ ፌዶሮቪች ዛቮልኑክ እንዲህ ብለዋል፦ “የክልሉን ሕጎችና ደንቦች በሙሉ አክብራችኋል፤ እንዲሁም ግንባታውን ያከናወናችሁት አስተዳደሩ የሰጠውን ፈቃድ ተከትላችሁ ነው። ይህ አምልኮ ቤት ለመንገዱም ሆነ ለሰፈሩ ውበት ሰጥቶታል። ለሠራችሁት ሥራ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።”

ይህ ድል መገኘቱ በተትዬቭ ከሚኖሩ ወንድሞቻችን ጋር እንድንደሰት ምክንያት ሆኖናል። ወንድሞቻችን ይሖዋን ለማወደስና ለማስከበር ይህን የስብሰባ አዳራሽ መጠቀም መቻላቸው ምንኛ የሚያስደስት ነው!—መዝሙር 69:30