በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 1, 2019
ዩክሬን

የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬን የመጽሐፍ ቅዱስ አውደ ርዕይ አደረጉ

የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬን የመጽሐፍ ቅዱስ አውደ ርዕይ አደረጉ

በሩሲያ ምልክት ቋንቋ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም መውጣቱን ተከትሎ ይህን ታሪካዊ የትርጉም ሥራ ለማስተዋወቅ የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬን የመጽሐፍ ቅዱስ አውደ ርዕይ አድርገዋል። አውደ ርዕዩ የጀመረው ጥቅምት 7, 2018 በለቪፍ ሲሆን እስከ ሰኔ 7, 2019 ድረስ ቆይቷል። አውደ ርዕዩ በካርኪፍ፣ ኪየቭ፣ ኦዴሳና ድኒፕሮ ከተሞችም ተካሂዷል።

በእያንዳንዱ ከተማ የተደረገው አውደ ርዕይ ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው ያሉ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች መስማት ለተሳናቸውና የመስማት ችግር ላለባቸው ሰዎች በወረቀትና በቪዲዮ ጥሪ አድርገው ነበር። በተጨማሪም የዩክሬን ቅርንጫፍ ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ዴስክ ለመምህራን፣ ለመገናኛ ብዙኃንና ለመንግሥት ባለሥልጣናት ግብዣ ልኮ ነበር።

የመጀመሪያው አውደ ርዕይ የተካሄደው በለቪፍ ከተማ በሚገኘው መስማት የተሳናቸው ሰዎች ክበብ ነበር፤ እዚያም እንደ JW Library Sign Language® ያሉ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የተዘጋጁ የኤሌክትሮኒክ ፕሮግራሞች ታይተው ነበር። ጎብኚዎች፣ ባለፉት ዘመናት ጥቅም ላይ የዋሉ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ፎርማቶችንም (ከጥቅልሎች አንስቶ እስከ ዘመናዊ መጽሐፍ) ተመልክተዋል። በ1927 ታትሞ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ በአውደ ርዕዩ ላይ ጉልህ ስፍራ ተሰጥቶት ነበር።

በሩሲያ ምልክት ቋንቋ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በመውጣቱ በጣም ተደስተናል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በሩሲያ ምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ ሰዎች ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ብለን እንተማመናለን።—ማቴዎስ 5:3