ሚያዝያ 24, 2024
ደቡብ አፍሪካ
የይሖዋ ምሥክሮች በደቡብ አፍሪካ ላሉ የቆሳ ተናጋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የሚያጽናና መልእክት ሰበኩ
ከጥር 29 እስከ መጋቢት 11, 2024 ኢስተርን ኬፕ በተባለው የደቡብ አፍሪካ ግዛት በቆሳ ቋንቋ በተካሄደው የስብከት ዘመቻ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ ከ11,000 በላይ ወንድሞችና እህቶች ተሳትፈዋል። በዚህ የአገሪቱ ግዛት ከሚኖሩት ሰባት ሚሊዮን ሰዎች አብዛኞቹ የቆሳ ተናጋሪዎች ናቸው። በውጤቱም ከ2,700 በላይ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው ጠይቀዋል።
በዘመቻው ወቅት ሁለት እህቶች ከሁለት ሳምንት በፊት ወንድሟን በአሳዛኝ አደጋ ያጣች አንዲት ሴት አገኙ። ሴትየዋ ስለ ወንድሟ አሟሟት እያለቀሰች ነገረቻቸው፤ እህቶች ራእይ 21:3, 4ን አውጥተው በማንበብ አጽናኗት። መጽሐፍ ቅዱስ ሞትና መከራ ስለሚወገድበት ጊዜ የሚሰጠውን ተስፋ ይበልጥ ማወቅ ስለፈለገች ስብሰባዎቻችን መቼና የት እንደሚካሄዱ እህቶችን ጠየቀቻቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትም ጀመረች።
ዙኪስዋ የተባለች እህት ከባድ የአርትራይተስ ሕመም ካለባት ሴት ጋር ውይይት ጀመረች። ሕመሟ ለልጆቿ ምግብ ማዘጋጀት ከባድ እንዲሆንባት አድርጓል። በዕለቱ የዳቦ ሊጥ ለማቡካት አቅም ስላጣች ለልጆቿ ምን እንደምታበላቸው ተጨንቃ ነበር። ዙኪስዋ ለሴትየዋ ስላዘነችላት ሊጥ ለማቡካት ራሷን አቀረበች፤ አብራት ያለችው እህት ደግሞ ለሴትየዋ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ነገረቻት። እህቶች ያሳዩዋት አሳቢነት ስለነካት ሴትየዋ ለጓደኞቿ ሁሉ ያደረጉላትን ነገር በደስታ ነገረቻቸው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች።
ሁለት ወንድሞች ቀቤራ ከተማ ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ሲሰብኩ አንድ እግሩ የተቆረጠ ሰው አገኙ። የሰውን ዘር የፈጠረው አምላክ ሆኖ እያለ ሰይጣን ዓለምን እንዲገዛ የፈቀደለት ለምን እንደሆነ ለረጅም ጊዜ ሲያሳስበው እንደቆየ ለወንድሞች ነገራቸው። (1 ዮሐንስ 5:19) ወንድሞቻችን መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩት። በዚያው ዕለት ትንሽ ቆይቶ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ ከተመለከተ በኋላ ሰውየው ከነባለቤቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የቀረበለትን ግብዣ በደስታ ተቀበለ።
እዚሁ ቀቤራ ከተማ ውስጥ አንዲት እህታችን ለአንዲት ሴት ከራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙር 37:29ን እንድታነብ ጋበዘቻት። ሴትየዋ ጥቅሱን ካነበበች በኋላ ሐሳቡ እንዳልገባት ተናገረች። ከዚያም እህት ጥቅሱን በቆሳ ከተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አነበበችላት። ሴትየዋ ተገርማ እንዲህ አለች፦ “እዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው ቆሳ በጣም ቀላል ነው። እኔ ከያዝኩት የመጽሐፍ ቅዱስ እትም የተሻለ ተረድቼዋለሁ።” በአሁኑ ወቅት በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናች ነው።
በመላው ደቡብ አፍሪካ ያሉ እጅግ ብዙ የቆሳ ተናጋሪ ሕዝቦች “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ በቃሉ ላይ ላሰፈረው የተስፋ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ በመሆናቸው እጅግ ተደስተናል።—2 ቆሮንቶስ 1:3