ነሐሴ 20, 2019
ደቡብ አፍሪካ
የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በክዋንያማ ቋንቋ አወጡ
ነሐሴ 16, 2019 በኦንዳንጓ፣ ናሚቢያ በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በክዋንያማ ቋንቋ መውጣቱ ተገለጸ። የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፍራንኮ ዳጎስቲኒ፣ በኦንዳንጓ የኤግዚቢሽን ማዕከል በተደረገው የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን አብስሯል።
የትርጉም ቡድኑ አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም መውጣቱ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በቀላሉ ማንበብና መረዳት እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ወንድሞችና እህቶች የይሖዋ ስም ወደ ትክክለኛው ቦታ ተመልሶ ሲያዩ በጣም እንደሚደሰቱ እርግጠኛ ነኝ።”
በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የክዋንያማ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 490 ገደማ አስፋፊዎች አሉ። እነዚህ አስፋፊዎች በዋነኝነት በአንጎላና በናሚቢያ ለሚኖሩት 1.4 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የክዋንያማ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይሰብካሉ።
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ ወይም በከፊል በ184 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ ከእነዚህ መካከል በ2013 በወጣው እትም ላይ ተመሥርተው ተሻሽለው የወጡ 25 ቋንቋዎችም ይገኙበታል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው የክዋንያማ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ በርካታ ሰዎች የአምላክን ቃል እንደሚሰብኩ ማወቃችን ያስደስተናል።—የሐዋርያት ሥራ 2:37