የካቲት 22, 2023
ደቡብ አፍሪካ
የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ የቬንዳ ቋንቋ የርቀት የትርጉም ቢሮ ከፈተ
ታኅሣሥ 7, 2022 በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ በማካዶ የቬንዳ ቋንቋ የርቀት የትርጉም ቢሮ ተከፍቷል። የትርጉም ቡድኑ፣ አሥር የሙሉ ጊዜ ተርጓሚዎችንና ለተወሰኑ ቀናት ብቻ የሚሠሩ ስምንት ተርጓሚዎችን ያቀፈ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን፣ ዚምባብዌ ውስጥ ደግሞ 100,000 የቬንዳ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዳሉ ይገመታል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ በአሁኑ ወቅት 800 ገደማ አስፋፊዎችን ያቀፉ 28 የቬንዳ ጉባኤዎች አሉ።
አሁን ቢሮው የሚገኝበት መሬት ላይ ቀደም ሲል ቤት ነበር፤ ቤቱ የማሻሻያ ሥራ ተደርጎለት አራት ራሳቸውን የቻሉ መኖሪያዎች እንዲይዝ ተደርጓል። ለትርጉም ቢሮዎቹ የሚውል አዲስ ሕንፃ ተገንብቷል። ተጨማሪ የመኖሪያ ስፍራ ለማግኘት ደግሞ በአቅራቢያው ካለ አፓርታማ ላይ ሦስት ቤቶች ተገዝተዋል።
የርቀት የትርጉም ቢሮው ንድፍ የአካባቢውን የአየር ጠባይ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። በአካባቢ ንድፍና ግንባታ ዲፓርትመንት ሥር የፕሮጀክቱ ኃላፊ ሆኖ የሠራው ወንድም ጆዲ ፓልቪ እንዲህ ብሏል፦ “ሞቃት የሆነውንና የሚወብቀውን የአየር ጠባይ ግምት ውስጥ በማስገባት ቀደም ሲል ግቢው ውስጥ የነበሩትን ትላልቅና ባለብዙ ቅጠል ዛፎች ባሉበት ትተናቸዋል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ዛፎች የማቀዝቀዝ ባሕርይ አላቸው። በተጨማሪም ሕንፃው ውስጥ ወለሉ በአብዛኛው በሴራሚክ ታይል የተሠራ ወይም ሊሾ የተደረገ ነው።”
ቢሮው እዚህ ቦታ መከፈቱ ተርጓሚዎቹ ከቋንቋው ተናጋሪዎች ጋር ይበልጥ የሚገናኙበት አጋጣሚ ፈጥሯል። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ሲል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “አሁን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከቋንቋው ተናጋሪዎች ጋር ብዙ እንገናኛለን። ይህም በትርጉም ችሎታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ነዋሪዎቹ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚጠቀሙባቸውን ቃላትና አባባሎች እንድንጠቀም ረድቶናል።” አንድ ሌላ ተርጓሚም እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ያለንበት ቦታ ለቪዲዮና ለድምፅ ቅጂ ልንጠቀምባቸው ከምንችል የቬንዳ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች ጋር አቀራርቦናል።”
እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለቬንዳ ተናጋሪ ማኅበረሰብ “የይሖዋን ውዳሴ [ለማስታወቅ]” ብዙ እየደከሙ ነው፤ ይሖዋም ጥረታቸውን መባረኩን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—መዝሙር 145:21