በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 13, 2019
ደቡብ አፍሪካ

ደቡብ አፍሪካ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም በሦስት ቋንቋዎች ወጣ

ደቡብ አፍሪካ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም በሦስት ቋንቋዎች ወጣ

መስከረም 6, 2019 በጆሃንስበርግ፣ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቬንዳ፣ በአፍሪካንስ እና በቆሳ ቋንቋዎች መውጣቱ ተገለጸ፤ እነዚህ ቋንቋዎች በድምሩ ከ16 ሚሊዮን የሚበልጡ ተናጋሪዎች አሏቸው። በኤፍ ኤን ቢ ስታዲየም ውስጥ ለታደሙት 36,865 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሶቹ መውጣታቸውን ያበሰረው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ነበር። ሌሶቶን፣ ናሚቢያንና ሴንት ሄለናን ጨምሮ በስምንት ሌሎች ቦታዎች የሚገኙ 51,229 ሰዎችም ፕሮግራሙን ተከታትለው ነበር።

መጽሐፍ ቅዱሶቹ ያሏቸውን ግሩም ገጽታዎች አስመልክቶ አንድ ተርጓሚ ሲናገር “ሁላችንም ልባችንን በሚነካው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አዲስ ማንበብ እንጀምራለን!” ብሏል። ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “[አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ] ያለው ዋነኛ ጥቅም ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን መሆኑ ነው፤ ምክንያቱም የአምላክን ስም ብዙ ቦታዎች ላይ ይጠቀማል።”

መጽሐፍ ቅዱሶቹ ለአገልግሎትም በጣም ጠቃሚ ናቸው። የቆሳ የትርጉም ቡድን አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም ለአገልግሎት ይጠቅመናል። ሰዎች ሰፊ ማብራሪያ ሳይሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት በቀላሉ መረዳት ይችላሉ።” አንድ የአፍሪካንስ ቋንቋ ተርጓሚ ደግሞ “አሁን የሚጠበቅብን ለሰዎች ጥቅሱን ማንበብ ብቻ ነው፤ ጥቅሱ ራሱን ያብራራል ሊባል ይችላል” በማለት ተናግሯል።

ወንድሞቻችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ የሚረዳቸው ለማንበብ ቀላል የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው ደስ ብሎናል።—ያዕቆብ 4:8