በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 5, 2023
ደቡብ ኮሪያ

የማቴዎስ መጽሐፍ በቻይንኛ ምልክት ቋንቋ ወጣ

የማቴዎስ መጽሐፍ በቻይንኛ ምልክት ቋንቋ ወጣ

ሚያዝያ 23, 2023 በደቡብ ኮሪያ በተካሄደ ፕሮግራም ላይ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ መጽሐፍ በቻይንኛ ምልክት ቋንቋ ወጣ። በቻይንኛ ምልክት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው። በደቡብ ኮሪያ ከሚገኙት ሁለት የቻይንኛ ምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች የመጡ 200 ገደማ ተሰብሳቢዎች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ነበር። አሁን ይህን ትርጉም ከ​jw.org እና ከ​JW Library Sign Language አፕሊኬሽን ላይ ማውረድ ይቻላል።

የትርጉም ቡድኑ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ፣ የቋንቋውን ተፈጥሯዊ ለዛ በጠበቀና ቅልብጭ ባለ መንገድ ለማስቀመጥ ጥረት አድርጓል። አንድ ተርጓሚ የትርጉም ሂደቱን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ከሦስቱ የትርጉም ቡድን አባላት ሁለቱ መስማት የተሳናቸው ናቸው፤ በመሆኑም መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስለሚያስቡበት መንገድ ብዙ ጊዜ እንወያይ ነበር። መስማት የተሳናቸው ሰዎች አብረውን መሥራታቸው ሥራውን ቀለል አድርጎልናል።”

ሌላ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ የትርጉም ሥራ መካፈሌ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ምን እንዳከናወነ፣ ምን ዓይነት ሕይወት እንዳሳለፈ እንዲሁም ምን እንዳስተማረ በግልጽ ለመረዳት አስችሎኛል።”

በፕሮግራሙ ላይ የተገኘ መስማት የተሳነው አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ከመውጣቱ በፊት በቻይንኛ ምልክት ቋንቋ የተተረጎሙት ጥቅሶች ጥቂት ነበሩ። ሁኔታው አንድን ትልቅ ሥዕል በጨረፍታ የማየት ያህል ነበር። አሁን የማቴዎስ መጽሐፍ ከወጣ በኋላ ግን ሙሉውን ሥዕል ለማየት ጓጉቻለሁ።”

መስማት የተሳነው ሌላ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ድርጅት የሚያዘጋጅልን የምልክት ቋንቋ ጽሑፎች፣ አሁን ደግሞ የማቴዎስ መጽሐፍ በቻይንኛ ምልክት ቋንቋ መውጣቱ ይሖዋ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ምን ያህል እንደሚወዳቸውና ሊረዳቸው እንደሚፈልግ አሳይቶኛል።”

በቅርቡ የወጣው ይህ መጽሐፍ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ማምለካቸውን እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል፤ ለዚህ ስጦታው ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—ዮሐንስ 4:24