ነሐሴ 7, 2023
ደቡብ ኮሪያ
የኮሪያ ቤቴል እድሳት ተጠናቀቀ
ፈቃደኛ ሠራተኞች ለአንድ ዓመት በዘለቀው ፕሮጀክት መካፈላቸው በዓለም አቀፍ የግንባታ ሥራ እንዲካፈሉ አዘጋጅቷቸዋል
ሠላሳ ዓመታትን ያስቆጠረው የኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ የመኖሪያ ሕንፃ እድሳት የተደረገለት ሲሆን ሥራው ሚያዝያ 30, 2023 ተጠናቋል። የቤቴል የመመገቢያ አዳራሽ እንዲሁም 62 የሚሆኑ የመኖሪያ ክፍሎች እድሳት ተደርጎላቸዋል። የእድሳቱ ዓላማ ሕንፃዎቹ ከበፊቱ የበለጠ ኃይል ቆጣቢ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፤ ይህም ከደህንነትም ሆነ ከምቾት አንጻር የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል። ለሥራው ራሳቸውን በፈቃደኝነት ካቀረቡት 170 ወንድሞችና እህቶች መካከል 71 የሚሆኑት በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክት ተካፍለው አያውቁም። ሆኖም የተሰጣቸውን ሥልጠና ሥራ ላይ በማዋላቸው እንዲሁም በኮሪያ ቤቴል እድሳት ሥራ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በመካፈላቸው ከ40 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች በሌሎች አገሮች በሚካሄዱ የቲኦክራሲያዊ ግንባታ ፕሮጀክቶች ለመካፈል ብቁ ሆነዋል።
እህት ኪም ሃ ዮን እንዲህ ብላለች፦ “በኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ የእድሳት ፕሮጀክት ላይ በሚገባ የተደራጀ ሥልጠና ስለተሰጠኝ አሁን በኢንዶኔዥያ በሚካሄደው የግንባታ ፕሮጀክት የመካፈል አጋጣሚ አግኝቻለሁ፤ የተማርኳቸውን ነገሮች እዚያ ፕሮጀክት ላይ የመጠቀም አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል።”
በኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት ሥራ ላይ የተካፈለ ሊ ምዮንግ ሁን የተባለ ወንድምም እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ፕሮጀክት ስካፈል በጣም ጠቃሚ ክህሎቶችን ተምሬያለሁ። የተሰጠኝ የሥራ ምድብ ከባድ ቢሆንም ድርጅቱ ያዘጋጃቸው የደህንነት መመሪያዎች እንዲሁም ያገኘሁት ሥልጠና ሥራውን ቀላል አድርጎልኛል።” በአሁኑ ጊዜ ወንድም ሊ በፊሊፒንስ እየተካሄደ ባለ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ በደስታ እየተካፈለ ይገኛል።
የኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት በመጠናቀቁ በጣም ደስ ብሎናል። በአሁኑ ጊዜ በሌሎች ቲኦክራሲያዊ ምድቦች እያገለገሉ ያሉትን ጨምሮ በፕሮጀክቱ የተካፈሉ ሁሉም ፈቃደኛ ሠራተኞች ያደረጉትን ጥረት መለስ ብለን ስናስብ ‘ለእምነት ሥራቸውና ከፍቅር ለመነጨ ድካማቸው’ እነሱን ለማመስገን እንነሳሳለን።—1 ተሰሎንቄ 1:3