ጥር 27, 2022
ደቡብ ኮሪያ
የኮሪያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አማራጭ አገልግሎቶች እንዲሻሻሉ ጠየቀ
አንድ የደቡብ ኮሪያ የሰብዓዊ መብቶች ባለሥልጣን በአገሪቱ ያለው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ያሉትን ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት መሥፈርቶች እንደማያሟላ በይፋ ገልጸዋል።
የኮሪያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን a አዲስ ኃላፊ የሆኑት ሶንግ ዱ ኋን ታኅሣሥ 2, 2021 በኮሚሽኑ ድረ ገጽ ላይ በአገሪቱ ያለው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት መሻሻል እንዳለበት የሚናገር መግለጫ አወጡ። ደቡብ ኮሪያ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ዝግጅት የጀመረችው ጥቅምት 26, 2020 ነው።
ኃላፊው ያወጡት መግለጫ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ በ2018 ካስተላለፈው ውሳኔ በኋላ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጥበት ዝግጅት ቢደረግም ይህ ዝግጅት ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት መሥፈርቶችን እንዲያሟላ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አምናለሁ . . .”
ኃላፊው ይህን መግለጫ ያወጡት፣ ከደቡብ ኮሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እና ከእስያ ፓስፊክ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ተወካዮች ጋር ኅዳር 23, 2021 ከተነጋገሩ በኋላ ነው። ወንድሞች በእስያ ፓስፊክ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር የተዘጋጀውን “አማራጭ የሲቪል አገልግሎት በደቡብ ኮሪያ—2021” የሚል ሪፖርት ለኃላፊው ሰጥተዋቸዋል።
ሪፖርቱ በደቡብ ኮሪያ ያለው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ መሥፈርቶችን እንደማያሟላ ይገልጻል። አማራጭ አገልግሎቱ የሚሰጠው ለ36 ወራት ሲሆን ይህም ወታደራዊ አገልግሎት ከሚሰጥበት ጊዜ በእጥፍ ይበልጣል። አማራጭ የሲቪል አገልግሎቱን የሚሰጡት ሰዎች የሚኖሩበት ሁኔታም ከእስረኞች አይተናነስም። በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በአሁኑ ወቅት የሚሠሩት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ነው። ሆኖም በመጀመሪያው ወር ከእስር ቤቱ ግቢ መውጣት አይችሉም። ከዚያ በኋላም ቢሆን መውጣት የሚችሉት ፈቃድ ከተሰጣቸው ብቻ ሲሆን ከምሽቱ 3:30 በፊት መመለስ ይጠበቅባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ያቀረቡትን አቤቱታ እያጤነ ይገኛል። ኮሚሽኑ የአገሪቱን ሕግ የመቀየር ሥልጣን ባይኖረውም ለሕግ አውጪ አካላት ሐሳብ ማቅረብ ይችላል።
በደቡብ ኮሪያ ያሉ ወንድሞቻችን በሚያሳዩት እምነትና ታማኝነት ተበረታተናል። ይሖዋ እንደሚደግፋቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 55:22
ልዩ ሪፖርት፦ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት በደቡብ ኮሪያ
a የኮሪያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በ2001 የተቋቋመ ለሰብዓዊ መብቶች የሚሟገት ድርጅት ነው።