በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 12, 2019
ደቡብ ኮሪያ

የኮሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳለፉት ያልተነገረ ታሪክ በብሔራዊ ሙዚየም ለእይታ ቀረበ

የኮሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳለፉት ያልተነገረ ታሪክ በብሔራዊ ሙዚየም ለእይታ ቀረበ

በኮሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳለፉት ታሪክ በብዙዎች ዘንድ አይታወቅም። አሁን ግን ታሪካቸው የኮሪያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው በቡሳን በሚገኝ አንድ ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ለእይታ ቀርቧል፤ ሙዚየሙ በጃፓን አገዛዝ ወቅት የውትድርና አገልግሎት እንዲሰጡ የተገደዱ ሰዎችን ታሪክ የሚያወሳ ነው። “ሕሊናቸውን ባለመቀየር ታሪክን ቀይረዋል” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ልዩ አውደ ርዕይ ኅዳር 12, 2019 ላይ የጀመረ ሲሆን ታኅሣሥ 13, 2019 ይደመደማል። አውደ ርዕዩ ከ80 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ኮሪያ በጃፓን ቅኝ ግዛት ሥር ሳለች የይሖዋ ምሥክሮች ስለወሰዱት የገለልተኝነት አቋምና በዚያ ምክንያት ስለደረሰባቸው ጭቆና ይናገራል።

ይህ አውደ ርዕይ መጀመሪያ ላይ የታየው መስከረም 2019 ሲሆን ቦታውም በሶል የሚገኘው የሶዴሙን እስር ቤት የታሪክ አዳራሽ a ነው። በአጠቃላይ 51,175 የሚያህሉ ጎብኚዎች ይህን አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል፤ ከእነዚህ መካከል በሶል በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ልዑክ ሆነው የሄዱ 5,700 ሰዎች ይገኙበታል።

ዱንግዴሳ በመባል የሚታወቀው ታሪካዊ ክስተት የተፈጸመው የይሖዋ ምሥክሮችና ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ከሰኔ 1939 እስከ ነሐሴ 1945 ባለው ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለው ወህኒ ቤት በተጣሉበት ወቅት ነው። እነዚህ ሰዎች የታሰሩት በንጉሠ ነገሥቱ አምልኮ ለመካፈል ፈቃደኞች ስላልሆኑና የፀረ-ጦርነት ፕሮፓጋንዳን የሚያስፋፉ ጽሑፎች ያሰራጫሉ ተብሎ ስለታሰበ ነው። በዚህም ምክንያት 66 ሰዎች ማለትም በወቅቱ በኮሪያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ማለት ይቻላል ለእስር ተዳርገዋል። የታሰሩት ሰዎች ከባድ ጫና ይደረግባቸው እንዲሁም ከፍተኛ አካላዊ ሥቃይ ይደርስባቸው ነበር። በእስር ቤት ውስጥ ከነበረው አስከፊ ሁኔታ የተነሳ ስድስት የይሖዋ ምሥክሮች በሕመም ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

በኮሪያ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ የሚከናወነውን ሥራ የሚያስተባብረው ወንድም ሆንግ ዴኢል እንዲህ ብሏል፦ “በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸው መጣስ የጀመረው ከ80 ዓመት በፊት በጃፓን አገዛዝ ሥር መሆኑን በኮሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች አያውቁም። ይህ ልዩ አውደ ርዕይ ይህን አስደናቂ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰዎች ማሳወቅ የሚቻልበት አጋጣሚ ከፍቷል።”

በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ሃን ሆንጉ የተባሉት የታሪክ ምሁር አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሰዎች አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ሰዎች ሕሊናቸውን በማክበር ጽኑ አቋም ለሚይዙ ሰዎች ዓይነተኛ ምሳሌ ናቸው። . . . ማኅበረሰባችን እንዲህ ላሉ ሰዎች ያለው አክብሮት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ባለበት በዚህ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ሊታወሱ የሚገባቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ናቸው።”

አውደ ርዕዩ የታሪክ ምሁራንንና የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቧል፤ ይህም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎች ስላሳለፉት ታሪክ ማኅበረሰቡን ለማስተማር ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል፤ ደግሞም ካለፈው ዓመት ወዲህ በኮሪያ ውስጥ ለዚህ ጉዳይ የሚሰጠው ትኩረት እየጨመረ መጥቷል። ሰኔ 28, 2018 ላይ የአገሪቱ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ የሚሰጥ አማራጭ አገልግሎት አለመቅረቡ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን እንደሆነ ገልጾ ነበር። ከአራት ወራት በኋላ ማለትም ኅዳር 1 ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን እንደ ወንጀል እንደማይቆጠር በየነ። እነዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በዚህ ምክንያት ታስረው የነበሩ በደቡብ ኮሪያ ያሉ ወንድሞቻችን እንዲፈቱና ለወታደራዊ አገልግሎት አማራጭ የሚሆኑ አገልግሎቶችን የሚመለከቱ ሕጎች እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።

በአውደ ርዕዩ ላይ የታዩት በኮሪያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሳዩት ጠንካራ እምነት እንዲሁም የማይናወጥ ድፍረት “ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” የሚሉትን የሚያጽናኑ ቃላት ያስታውሱናል።—መዝሙር 118:6

a የታሪክ አዳራሹ የሙዚየምነት አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት እስር ቤቱ ከ1960ዎቹ እስከ 1980ዎቹ ባለው ጊዜ ውስጥ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ለማሰር ያገለግል ነበር

 

በሶል፣ ኮሪያ የሚገኘው የሶዴሙን እስር ቤት የታሪክ አዳራሽ። መስከረም 2019 ላይ አውደ ርዕዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው እዚህ ነው

ወጣት ተማሪዎች የዱንግዴሳ ክስተት አውደ ርዕይ ከቀረበበት የታሪክ አዳራሽ ውጭ ተሰብስበው፤ በአጠቃላይ 51,175 ሰዎች አውደ ርዕዩን ጎብኝተዋል

አውደ ርዕዩ የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ቤት ሳሉ ይጠቀሙበት የነበረውን መጠበቂያ ግንብ ሞዴል የሚያሳይ ክፍል አለው

የይሖዋ ምሥክሮች ይታሰሩ የነበረበትን አስከፊ ሁኔታ ለማሳየት የተቀመጡ በሰው ቅርጽ የተሠሩ አምስት ምስሎች

በጃፓን አገዛዝ ወቅት የውትድርና አገልግሎት እንዲሰጡ የተገደዱ ሰዎችን ታሪክ የሚያወሳው በቡሳን የሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም በአሁኑ ወቅት አውደ ርዕዩን እያሳየ ይገኛል

አውደ ርዕዩ የሚደመደመው ፖለቲካዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት ከታሰሩት 66 ሰዎች መካከል የአንዳንዶቹን ታሪክ የሚያሳዩ የግድግዳ ፎቶዎችን በማቅረብ ነው