መጋቢት 3, 2021
ደቡብ ኮሪያ
የኮሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጠባባቂ የጦር ሠራዊት ውስጥ ሥልጠና ለመውሰድ በሕሊና ምክንያት ፈቃደኛ አለመሆን ወንጀል እንዳልሆነ ወሰነ
ጥር 28, 2021 የደቡብ ኮሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጠባባቂ የጦር ሠራዊት ውስጥ ሥልጠና ለመውሰድ በሕሊና ምክንያት ፈቃደኛ አለመሆን ወንጀል እንዳልሆነ ወሰነ። ይህ ውሳኔ፣ የይሖዋ ምሥክር ከመሆናቸው በፊት በጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ ወንድሞቻችን በተደጋጋሚ ቅጣት እንዳይበየንባቸው ያደርጋል።
በጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ የደቡብ ኮሪያ ወንዶች በሙሉ ለስምንት ዓመት ያህል ለተጠባባቂ የጦር ሠራዊት አባላት የሚሰጠውን ሥልጠና በየተወሰነ ጊዜ መከታተል አለባቸው። ስለዚህ ቀደም ሲል ወታደሮች የነበሩ ወንድሞቻችን ሥልጠናውን እንዲወስዱ በተደጋጋሚ ይጠራሉ፤ እንዲሁም ይህን ሥልጠና ለመከታተል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በተደጋጋሚ ይቀጣሉ። አንድ ወንድም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 60 ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ፣ አቃቤ ሕግ ቢሮ፣ ፍርድ ቤት እና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
በ2018 የኮሪያ ሁለት ፍርድ ቤቶች ይኸውም የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን ወንጀል እንዳልሆነ ወሰኑ፤ በተጨማሪም አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መንገድ ቀየሱ። ይሁንና ፍርድ ቤቶቹ የተጠባባቂ የጦር ሠራዊት ሕግን በተመለከተ ምንም ውሳኔ አላሳለፉም፤ ይህ ሕግ በተጠባባቂ የጦር ሠራዊት ውስጥ ሥልጠና ለመውሰድ በሃይማኖታዊ እምነታቸው ምክንያት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች እንዲቀጡ ያደርጋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ ያሳለፈው ውሳኔ፣ በተጠባባቂ የጦር ሠራዊት ውስጥ ሥልጠና ለመውሰድ በሕሊና ምክንያት ፈቃደኛ አለመሆን እንደሚቻል ይገልጻል። ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የፍርድ ቤት ሙግት የነበራቸው ወንድሞቻችን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው መቀጣትና መታሰር ቀርቶላቸዋል፤ ከዚህ ይልቅ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ። ይህ ብይን በተላለፈበት ወቅት ተከሳሽ ሆነው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ወንድሞች አንዱ የሆነው ናም ቴ ሂ እንዲህ ብሏል፦ “ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ከቀረብኩ በኋላ በመጨረሻ መብቴ ተከበረልኝ። ትልቅ ሸክም ከላዬ እንደወረደልኝ ተሰምቶኛል።”
‘በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖራቸው ሲሉ መከራን ችለው ካሳለፉትና ግፍ ከደረሰባቸው’ የኮሪያ ወንድሞቻችን እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነን እንደሰታለን፤ ይሖዋንም እናመሰግናለን!—1 ጴጥሮስ 2:19