በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከላይ በስተ ግራ አንስቶ ዙሪያውን፦ መድረኩ፣ ተሰብሳቢዎቹ እንዲሁም ቴክኒክ ላይ የሠሩ ወንድሞች። ወንድም ማርክ ሳንደርሰን ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ፣ ከጥቃቱ ከተረፉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲያወራ። የስብሰባው ፕሮግራም። ካርዶችና የሚያጽናኑ ደብዳቤዎች። የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወቱት የይሖዋ ምሥክሮች መድረክ ላይ መዝሙሩን ሲጫወቱ። ወጣት እህቶች ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ እርስ በርስ ሲጽናኑ። የፖሊስ እና የእሳት አደጋ ተወካዮች ፕሮግራሙ እስኪጀምር ሲጠባበቁ

ሚያዝያ 10, 2023
ጀርመን

በሃምበርግ በተከፈተው ተኩስ ለተጎዱት በተዘጋጀው የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኙ

በሃምበርግ በተከፈተው ተኩስ ለተጎዱት በተዘጋጀው የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኙ

መጋቢት 9, 2023 በሃምበርግ፣ ጀርመን ባለ አንድ የስብሰባ አዳራሽ የተከፈተው ተኩስ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን በጥልቅ ያሳዘነ ክስተት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን፣ የሕትመት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ወንድም ጋይዩስ ግሎከንቲን እንዲሁም የማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለማጽናናትና ለማበረታታት ወደ ሃምበርግ ተጉዘው ነበር። የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ለማሰብ መጋቢት 25 በከተማዋ ባለ አንድ የስፖርት ስታዲየም ውስጥ ስብሰባ ተደረገ። ይህን ልብ የሚነካ ፕሮግራም የተመለከቱ ሁሉ፣ ይህ ዝግጅት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያለቅሱትን የማጽናናትና የማበረታታት ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ብዙዎች፣ ከጥቃቱ የተረፈ አንድ ወንድም የተናገረውን ሐሳብ ይጋራሉ፤ ወንድም “ዛሬ ይሖዋ እቅፍ እንዳደረገን ተሰምቶናል” በማለት ተናግሯል።

ከ3,300 የሚበልጡ ሰዎች በፕሮግራሙ ላይ በአካል ተገኝተዋል። ከ90,000 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቀጥታ ስርጭት ተከታትለዋል።

ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን በተጨማሪ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ተወካዮች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። ከእነዚህም መካከል የሃምበርግ ከተማ ከንቲባና ምክትል ከንቲባ፣ የሃምበርግ ከተማ ፓርላማ ፕሬዚዳንት፣ በሃምበርግ የዩናይትድ ስቴትስ ዋና ቆንስላ፣ የውስጥ ጉዳዮችና የስፖርት ባለሥልጣን፣ የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ፣ የሃምበርግ ዋና የፖሊስ አዛዥ እንዲሁም የፖሊስ ምክትል ፕሬዚዳንት ይገኙበታል።

ተሰብሳቢዎችና የሙዚቃ መሣሪያዎችን የሚጫወተው ቡድን አባላት “የአምላክ ድንቅ ሥራዎች” የሚለውን መዝሙር አብረው ሲዘምሩ

ፕሮግራሙ የተጀመረው የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች የሙዚቃ መሣሪያዎች በተጫወቱት መዝሙር ነው። የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው የማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዮአኪም ሸቭዤክ ነው። ወንድም ሸቭዤክ፣ የመታሰቢያ ንግግሩን እንዲያቀርብ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነውን ወንድም ደርክ ቹፔክን ወደ መድረክ ጋበዘ። ቀጥሎም ወንድም ቹፔክ፣ ወንድም ሳንደርሰንን ወደ መድረክ የጋበዘ ሲሆን ወንድም ሳንደርሰንም አጠር ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር አቀረበ። ከዚያም ወንድም ቹፔክ በድጋሚ ወደ መድረክ በመውጣት የመደምደሚያውን ንግግር አቀረበ። ፕሮግራሙ የተጠናቀቀው ወንድም ግሎከንቲን ባቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎትና በመዝሙር ነው።

ወንድም ሳንደርሰን በንግግሩ ላይ፣ አምላክ እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ነገሮችን እንደማያመጣ ጠቀሰ። ይልቁንም መክብብ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው እነዚህ ነገሮች “ያልተጠበቁ ክስተቶች” እንደሆኑ ተናገረ። (መክብብ 9:11) ወንድም ሳንደርሰን እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ካሉት የጭካኔ ድርጊቶች ወይም ድንገተኛ ክስተቶች በስተ ጀርባ ያለውን ምክንያት ለማግኘት ጥረት ማድረግ አይኖርብንም። . . . ተስፋችን፣ እምነታችን እንዲሁም ፍቅራችን አሳዛኝ ሁኔታዎችን አልፎ መሄድ ይችላል። እነዚህ ሦስት ባሕርያት በጥላቻና በዓመፅ ላይ ድል መቀዳጀት ይችላሉ።” በተጨማሪም ወንድም ሳንደርሰን፣ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ላደረጉት ድጋፍ ፖሊሶችን፣ የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ሰጪ ተቋማትን እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎችን አመስግኗቸዋል።

ወንድም ደርክ ቹፔክ

ወንድም ቹፔክ ባቀረበው ልብ የሚነካ ንግግር ላይ እንዲህ ብሏል፦ “መጋቢት 9 የተፈጸመው ጥቃት በተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ የተፈጸመ ጥቃት አይደለም። በሁላችንም ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው። ዛሬ እዚህ የተገኘነው ለጥላቻና ለዓመፅ መልስ ለመስጠት ነው። መልሱ ፍቅር፣ ርኅራኄና አዘኔታ እንዲሁም ተስፋና እምነት እንደሆነ ማሳየት እንፈልጋለን። ቅዱሳን መጻሕፍት ‘በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ’ የሚል ምክር ይሰጡናል። የእኛም ቁርጥ ውሳኔ ይህ ነው። ዛሬ እዚህ የመጣነውም ለዚህ ነው።”—ሮም 12:21

ወንድም ቹፔክ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን አንድ በአንድ በስም እየጠራ የሚከተለውን ሐሳብ ሲናገር ታዳሚዎቹ በጣም ስሜታዊ ሆነው ነበር፦ “የመጣነው ስቴፋንን፣ ሴባስትያንን፣ ጄምስን እና ማሪን፣ ስቴፋኒን፣ ዳንን እንዲሁም ሕፃኑን ሮሚን (በእናቱ ማህፀን ውስጥ ሆኖ ሕይወቱ ያለፈው ፅንስ) ለመሰናበት እንዲሁም ለማስታወስ ጭምር ነው።” በስብሰባው ላይ ለተገኙት ከጥቃቱ የተረፉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ለሟቾች ቤተሰቦች “ውድ ቤተሰቦች፣ ከእናንተም ጎን መቆም እንፈልጋለን” በማለት ተናግሯል።

ስሜት ቀስቃሽ በሆነው የንግግሩ መደምደሚያ ላይ በሕይወት የተረፉት ወዳጆቻቸው የሚናፍቋቸውን የሟቾቹን ባሕርያት ጠቅሷል። ራእይ 21:4, 5⁠ን መሠረት በማድረግ የሚከተለውን ሐሳብ ተናግሯል፦ “አዎ፣ የሞቱ ወዳጆቻችን ይናፍቁናል። ሐዘኑ ያስለቅሰናል። የተለዩን ሰዎች ምንጊዜም ከውስጣችን አይወጡም። ሆኖም አምላካችን አሁን የሚሰማንን ሐዘን ለዘለቄታው የሚያስወግድበት ቀን ይመጣል፤ ይህን ሁሉ ያስወግድልናል። . . . ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም። ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ ያስተማሩት ይህን ነው። የእኛም ተስፋ ይህ ነው። ሞት ድል ይደረጋል። የመጨረሻውን ምዕራፍ የሚዘጋው ሞት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላካችን ነው። . . . የስቴፋን፣ የሴባስትያን፣ የጄምስ እና የማሪ፣ የስቴፋኒ፣ የዳን እንዲሁም የሕፃኑ የሮሚ የመጨረሻ ምዕራፍ ገና አልተዘጋም።”

የሃምበርግ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ዶክተር ፒተር ቼንቸር

ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ከመንግሥት ባለሥልጣናቱ መካከል አንዳንዶቹ መግለጫ ሰጥተው ነበር። የሃምበርግ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ዶክተር ፒተር ቼንቸር እና የሃምበርግ ከተማ ፓርላማ ፕሬዚዳንት የሆኑት ወ/ሮ ካሮላ ፋይት በተናጠል በሰጡት መግለጫ ላይ ለሟቾቹ ወዳጅ ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልጸዋል። ዶክተር ቼንቸር፣ ከጥቃቱ የተረፉት ሰዎች “ጠንካራ ክርስቲያናዊ እምነት” ስላላቸው “ሐዘናቸውንና ጉዳታቸውን ድፍረት በተሞላበት መንገድ እየተቋቋሙ” እንዳሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም የጀርመን ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከአቶ ፍራንክ ቫልተር ሽታየንማየር የተላከ የማጽናኛ ደብዳቤ አንብበዋል።

የሃምበርግ ከተማ ፓርላማ ፕሬዚዳንት የሆኑት ወ/ሮ ካሮላ ፋይት

በርካታ የዜና ዘጋቢዎች በቦታው በመገኘት ስለ ፕሮግራሙ ዘግበዋል። በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሠራ ሰው “እዚህ ያሉት ሰዎች በሙሉ የሚያሳዩት ደግነት አስደናቂ ነው” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በብዙ ፕሮግራሞች ላይ ተገኝተናል። እንደዚህ ያለ ነገር ግን የትም አላየንም፤ ንግግሮቹ የቀረቡበት መንገድም ሆነ የተጠቀሱት ሐሳቦች ልዩ ናቸው።”

ከጥቃቱ የተረፉ አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “በተስፋችን ላይ ማሰላሰል እንዲሁም ይህን የሐዘን ጊዜ በብዙ ወንድሞች ተከበን ማሳለፍ መቻላችን በጣም ትልቅ ነገር ነው።”

ተኩሱ በተከፈተበት የስብሰባ አዳራሽ የሚሰበሰብ ሌላ ጉባኤ ያለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከሐዘኑ ቶሎ መጽናናት አልቻልኩም። እዚህም የመጣሁት በሐዘን በጣም ዝዬ ነው። ሆኖም ፕሮግራሙ ክብር የተላበሰ ነበር። . . . ወንድሞች እንዲሁም ተወካይ ሆነው የመጡት ባለሥልጣናት የሰጧቸው ሐሳቦች ሐዘናችን በጥልቅ እንደተሰማቸው የሚያሳዩ ናቸው።”

የመታሰቢያው ፕሮግራም የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ በግልጽ የሚያሳይ ነበር። “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ፣ በሃምበርግ በተፈጸመው ጥቃት በጥልቅ የተጎዱትን ሁሉ መደገፉን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—2 ቆሮንቶስ 1:3

 

የማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባልና የስብሰባው ሊቀ መንበር የሆነው ወንድም ዮአኪም ሸቭዤክ መድረክ ላይ። ሙዚቃውን የተጫወቱት የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የሙዚቃ ባለሙያዎች ከጀርባው ተቀምጠዋል

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን የሚያጽናና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ሲያቀርብ፤ ንግግሩ ወደ ጀርመንኛ ተተርጉሟል

የመንግሥት ባለሥልጣናት ከፊት ተቀምጠው ንግግሮቹን ሲያዳምጡ

ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ወንድሞችና እህቶች አብረው ጊዜ ሲያሳልፉና እርስ በርስ ሲበረታቱ

በስታዲየሙ የእንግዳ መቀበያ ቦታ ላይ የተቀመጡ ካርዶችና የሚያጽናኑ ደብዳቤዎች

በስታዲየሙ የእንግዳ መቀበያ ቦታ አንድ የጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት አንዳንዶቹን በቅርበት ለሚያውቅ በሃምበርግ የሚኖር የጉባኤ ሽማግሌ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግለት