በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኦራንየንቡርግ፣ ጀርመን የሚገኘው ዛክሰንሃውዘን መታሰቢያ እና ሙዚየም። ውስጠኞቹ ፎቶግራፎች፦ ጎብኚዎች “የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል” የተባለውን አዲስ ልዩ አውደ ርዕይ ሲጎበኙ

ኅዳር 4, 2024
ጀርመን

በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ያልተሳተፉ ሰዎችን ለመዘከር በጀርመን ዛክሰንሃውዘን መታሰቢያ እና ሙዚየም ውስጥ አውደ ርዕይ ተዘጋጀ

በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ያልተሳተፉ ሰዎችን ለመዘከር በጀርመን ዛክሰንሃውዘን መታሰቢያ እና ሙዚየም ውስጥ አውደ ርዕይ ተዘጋጀ

ኣውጉስት ዲክማን

መስከረም 15, 2024 ኦራንየንቡርግ፣ ጀርመን የሚገኘው ዛክሰንሃውዘን መታሰቢያ እና ሙዚየም “የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል” በሚል ርዕስ ጊዜያዊ አውደ ርዕይ ከፍቷል። እስከ ታኅሣሥ 2024 አጋማሽ ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆየው ይህ አውደ ርዕይ የጀመረበት ዕለት፣ ወንድም አውጉስት ዲክማን ከተገደለ 85ኛ ዓመቱን ካስቆጠረበት ዕለት ጋር ተመሳሳይ ነው። ኣውጉስት፣ ሕሊናቸው ለጦርነት ለመሰለፍ እንደማይፈቅድላቸው በመግለጻቸው ከተገደሉ በስም የሚታወቁ የናዚ አገዛዝ ሰለባዎች መካከል የመጀመሪያው ነው።

ገርሃርድ ሌብሆልድ እና ኤሚ ጸህደን

የናዚ አገዛዝ፣ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ሞት የተፈረደባቸው ከ280 በላይ የይሖዋ ምሥክሮችን ገድሏል። ከእነዚህ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ውስጥ የአንዳንዶቹን ታሪክ የሚዘክሩ ጽሑፎችና ፎቶግራፎች በአውደ ርዕዩ ላይ በነበሩት 33 ማሳያዎች ላይ ቀርበዋል። ለእይታ ከቀረቡት ተሞክሮዎች መካከል የእህት ኤሚ ዜደን (ጸህደን) ተሞክሮ ይገኝበታል። እህት ኤሚ ሰኔ 9, 1944 በበርሊን፣ ጀርመን በሚገኘው ፕሎትሰንዜ እስር ቤት ተገድላለች፤ እህታችን ሞት የተፈረደባት የጉዲፈቻ ልጇን ሆርስትን ጨምሮ ገርሃርድ ሌብሆልድ እና ቨርነር ጋስነር የተባሉትን ወንድሞች በድፍረት በመደበቋ ምክንያት ነው። ሦስቱም ወንድሞች ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም።

ዮዜፍ ሬቫልድ

ወንድም ሃንስ-ዮኣኺም ሬቫልድ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በተደረገለት ቃለ መጠይቅ ስለ አባቱ ስለ ዮዜፍ ተናግሮ ነበር። ዮዜፍ፣ በ1938 የጀርመንን ሠራዊት ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተነሳ በቁጥጥር ሥር ውሎ የአንድ ዓመት እስራት ተፈረደበት። ከጊዜ በኋላ ዛክሰንሃውዘንን ጨምሮ በሦስት ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስሯል። ኣውጉስት ዲክማን በተረሸነበት ጊዜም የዓይን ምሥክር ነበር። ከዚህ ሁሉ ስደት በኋላም ዮዜፍ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ካደረገው ቁርጥ ውሳኔ ፍንክች አላለም። አንድ ወንድም አውደ ርዕዩን ከጎበኘ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በወቅቱ የነበሩት ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ገለልተኝነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ማንኛውንም መከራ ለመቀበል ሌላው ቀርቶ ሕይወታቸውን እንኳ ለመስጠት ፈቃደኞች እንደነበሩ ስመለከት በጣም ነው የተደነቅሁት። እኔም እንደ እነሱ ዓይነት ቁርጠኝነት ማሳየት እፈልጋለሁ።”

የናዚን አገዛዝ ተቋቁመው ለጸኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጥልቅ አክብሮት አለን። በአሁኑ ወቅትም ቢሆን ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው የተነሳ ቀጥተኛ ስደት ይደርስባቸዋል፤ እነዚህ ድንቅ የታማኝነት ምሳሌዎች፣ መከራ ሲያጋጥመን ይሖዋ እንደሚደግፈንና እንደሚያጠነክረን እንድንተማመን ያደርጉናል።​—1 ጴጥሮስ 5:10