በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 23, 2021
ጀርመን

የማቴዎስና የዮሐንስ መጻሕፍት በጀርመንኛ ምልክት ቋንቋ ወጡ

የማቴዎስና የዮሐንስ መጻሕፍት በጀርመንኛ ምልክት ቋንቋ ወጡ

የማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ደርክ ግሩንድማን ታኅሣሥ 18, 2021 የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ክፍሎች በጀርመንኛ ምልክት ቋንቋ መውጣታቸውን አበሰረ። ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች ፕሮግራሙን በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት ተከታትለዋል።

የጀርመን መንግሥት፣ ጀርመንኛ ምልክት ቋንቋን እንደ ቋንቋ ቆጥሮ እውቅና የሰጠው በ2002 ነው። በጀርመን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ግን በትላልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ ንግግሮችን ወደ ምልክት ቋንቋ ማስተርጎም የጀመሩት ከ1960ዎቹ አንስቶ ነው። በዛሬው ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ በ11 የጀርመንኛ ምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና በ21 ቡድኖች የታቀፉ 571 አስፋፊዎች አሉ።

በ1973 በሙኒክ፣ ጀርመን በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንድ ወንድም ፕሮግራሙን ወደ ምልክት ቋንቋ ሲያስተረጉም

ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ወደ ጀርመንኛ ምልክት ቋንቋ ተተርጉመው ሲወጡ ይህ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ በፊት አስፋፊዎች ለግል ጥናታቸውም ሆነ ለአገልግሎታቸው ማግኘት የሚችሉት በተናጠል የተተረጎሙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ብቻ ነበር።

አንድ አስፋፊ “የተለያዩ ጥቅሶች እንጂ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረንም፤ በዚህ የተነሳ ብዙ ጊዜ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ወይም እምነታችንን የሚደግፉ ማስረጃዎችን ለማግኘት እንቸገር ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን በየዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰነ ነገር እንዲያነብቡ ማበረታታትም ይከብደን ነበር፤ ምክንያቱም በተናጠል የወጡትን ጥቅሶች መመልከት ቀላል አይደለም” ብሏል።

የጀርመንኛ ምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን አባላት በስቱዲዮአቸው ውስጥ ቪዲዮ ሲቀርጹ

አንድ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎምና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት መቻል በጣም ያስደስታል። በዚህ ፕሮጀክት የመካፈል መብት በማግኘታችን ልባችን ተነክቷል።”

በጀርመንኛ ምልክት ቋንቋ የወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም ቅን ልብ ያላቸው ሌሎች በርካታ ሰዎች የይሖዋን መንገድ እንዲማሩ ይረዳ ዘንድ ጸሎታችን ነው።—መዝሙር 25:9