ታኅሣሥ 27, 2022
ጀርመን
የይሖዋ ምሥክሮች ከአነማሪ ኩሰሮ ማኅደር ጋር በተያያዘ በጀርመን አዲስ ክስ መሠረቱ
የአነማሪ ማኅደር ለይሖዋ ምሥክሮች ሊሰጥ እንደሚገባ የሚጠቁም አዲስ ማስረጃ ተገኘ
ከዚህ ቀደም jw.org እና ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ እንደተዘገበው ድሬዝደን፣ ጀርመን የሚገኘው የቡንደስቬር ወታደራዊ ታሪክ ሙዚየም የእህት አነማሪ ኩሰሮን ማኅደር ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ይህ ድርጊት የእህት አነማሪን ኑዛዜ የሚጥስ ነው። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮችን አቋም የሚደግፍ አዲስ ሰነድ በቅርቡ ተገኝቷል። በመሆኑም ድርጅታችን በሙዚየሙ ላይ አዲስ ክስ መሥርቷል።
የይሖዋ ምሥክሮች ከሰባት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ማኅደሩን ከሙዚየሙ ለማግኘት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድርድር ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል። በመሆኑም ድርጅታችን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደው። የሚያሳዝነው በ2021 ፍርድ ቤቱ ጥያቄያችንን ውድቅ አደረገው፤ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው ‘ሙዚየሙ ግዢውን ያከናወነው በተገቢው መንገድ ነው’ በማለት ነው።
ታሪካዊ ቅርስ
አነማሪ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ እልቂት ወቅት ከደረሰባቸው ነገር ጋር የተያያዙ ሰነዶችን በጥንቃቄ ማሰባሰብ የጀመረችው በ26 ዓመት ዕድሜዋ ነው። በ2005 ሕይወቷ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ይህን ማኅደር ከ65 ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ጠብቃ አቆይታዋለች፤ ይህን በማድረጓ ሕይወቷ አደጋ ላይ የወደቀበት ጊዜም ነበር። ለቀጣይ ትውልድ በተለይም ለእምነት አጋሮቿ ብላ ያቆየችው ይህ ማኅደር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ሰዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ታሪካዊ ቅርስ ነው።
አነማሪ ይህን ማኅደር ያደራጀችው፣ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ ሌሎች በርካታ ሰዎች ከቤተሰቧ የታማኝነት ታሪክ ትምህርት እንዲያገኙ በማሰብ ነው። ይህን ዓላማዋን ለማሳካት ስትል የማኅደሩ ብቸኛ ወራሽ ያደረገችው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅትን ነው። ኑዛዜዋ ግን እስካሁን አልተፈጸመም።
በ1991 በወጣው ፐርፕል ትራያንግልስ በተባለው የብሪታንያ ዘጋቢ ፊልም ላይ አነማሪ፣ ሁለት ወንድሞቿና ሁለት እህቶቿ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ነበር። ይህ ዘጋቢ ፊልም በኩሰሮ ቤተሰብ ላይ ያተኮረ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን ለመካድና ሂትለርን ለመደገፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ በናዚ አገዛዝ የደረሰባቸውን ስደት ይዘግባል። በፊልሙ ላይ አነማሪ፣ የተለያዩ ሰነዶችንና ፎቶግራፎችን የያዘውን ይህን ማኅደር ይዛ ትታያለች።
አነማሪ ሕይወቷ ከማለፉ ጥቂት ቀደም ብሎ በተደረገላት ቃለ መጠይቅ ላይ፣ በአንድ ወቅት ጌስታፖ በምትኖርበት አፓርታማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏትና በዚህ ወቅት አንዳንድ አስፈላጊ ሰነዶች ሊወሰዱባት እንደነበር ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሄን ቦርሳ መግቢያው ጋ አስቀምጬው ነበር። ከበታቹ አንዳንድ ደብዳቤዎችንና ሌሎቹን ሰነዶች በሙሉ አስቀመጥኳቸው።” ከዚያም አነማሪ ቦርሳውን በፖም ሞላችው፤ ይህን ያደረገችው ፈታሾቹ ከቦርሳው ሥር ምን እንዳለ ለማየት እንዳይሞክሩ ለማድረግ ስትል ነው። ምናልባት ዕቅዷ ባይሳካ ፖሙ ለእስር ቤት ቀለብ እንደሚሆናት አስባ ነበር። ጥሩነቱ ዕቅዷተሳካ።
ያለፈቃድ የተካሄደ ሽያጭ
አነማሪ ከሞተች ብዙም ሳይቆይ ማኅደሩ ከቤቷ ጠፋ። በኋላ ላይ እንደተደረሰበት የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ያቆመ አንድ ወንድሟ ማኅደሩን ለሙዚየሙ ሸጦት ነበር። አነማሪ ወንድሟ እንዲህ እንዲያደርግ ጨርሶ ፈቃድ አልሰጠችውም። ይህ ወንድሟ አሁን በሕይወት የለም።
አሁን በሕይወት ያሉትና የአነማሪን ኑዛዜ በደንብ የሚያውቁት የቤተሰቧ አባላት፣ ፍርድ ቤቱ ማኅደሩ ሙዚየሙ ውስጥ እንዲቆይ መወሰኑ በጣም አስደንግጧቸዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአነማሪ ቤተሰብ አባላት፣ ወዳጆቿና በናዚ ስደት የደረሰባቸው ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ለሙዚየሙና ሙዚየሙን ለሚያስተዳድረው የመከላከያ ሚኒስቴር በመቶዎች የሚቆጠሩ ደብዳቤዎችን ጽፈዋል፤ በደብዳቤያቸው ላይ፣ አነማሪ በተናዘዘችው መሠረት ማኅደሩ ለይሖዋ ምሥክሮች እንዲመለስ ጠይቀዋል።
ልዩ ቅርስ
በማኅደሩ ውስጥ ካሉት መተኪያ የሌላቸው ሰነዶች መካከል፣ የአነመሪ ወንድም ቪልሄልም ሚያዝያ 26, 1940 የጻፈው የስንብት ደብዳቤ ይገኝበታል። ቪልሄልም የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኑ መጠን ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም። በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የናዚ መንግሥት ሞት ፈረደበት።
ቪልሄልም የጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ “የተወደዳችሁ ወላጆቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ፦ ምን ያህል እንደምወዳችሁ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፤ የቤተሰባችንን ፎቶግራፍ ባየሁ ቁጥር ይህን አስታውሳለሁ። ቤታችን ሁልጊዜ ሰላም የሰፈነበት ነበር። ያም ቢሆን መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘን ከሁሉም በላይ አምላክን መውደድ አለብን። ከእሱ ጎን ከተሰለፍን ወሮታችንን ይከፍለናል።” ቪልሄልም ሚያዝያ 27 ማለዳ ላይ በ25 ዓመቱ ተረሸነ።
የአነማሪ ወላጆች የሆኑት ፍራንትስ እና ሂልዳ 11 ልጆች ወልደዋል። እንደ ቪልሄልም ሁሉ ፍራንትስ እና የመጀመሪያዎቹ ወንዶች ልጆች በጦርነቱ ተካፋይ ለመሆን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለእስር ተዳርገዋል። ትናንሾቹ ልጆች ደግሞ “ሃይል ሂትለር” የሚለውን ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከወላጆቻቸው ተነጥለው የተሃድሶ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደረጉ፤ በኋላ ላይ ደግሞ ለአሳዳጊ ቤተሰብ ተሰጡ።
ከኩሰሮ ቤተሰብ ወንዶች ልጆች አንዱ የሆነው ቮልፍጋንግ፣ በወታደራዊ ችሎት ፊት በቀረበበት ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን የአምላክ ሕግ ተምሬ ያደግሁ የይሖዋ ምሥክር ነኝ። አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ሕግጋት ሁሉ የሚበልጠውና እጅግ ቅዱስ የሆነው ሕግ ‘አምላክህን ከምንም ነገር በላይ አስበልጠህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው። ሌላው ትእዛዝ ደግሞ ‘አትግደል’ ይላል። ታዲያ ፈጣሪያችን ይህን ሁሉ ያስጻፈው ለዛፎች ይመስላችኋል?”
ቮልፍጋንግ መጋቢት 28, 1942 በ20 ዓመቱ በጊሎቲን አንገቱ ተቀልቶ ተገደለ።
የእምነት ፈተና
አነማሪ እና ቤተሰቧ በአምላክ ላይ ባላቸው እምነትና የናዚን ጦርነት ለመደገፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፤ ሌሎችን ከመግደል ይልቅ ለመሞት መርጠዋል። የዚህ ቤተሰብ አባላት በድምሩ 47 ዓመታትን በእስር አሳልፈዋል።
የአነማሪ ማኅደር የዚህን ቤተሰብ ግሩም የእምነት ምሳሌ ሕያው በሆነ መንገድ ያሳያል። በማኅደሩ ውስጥ የተካተቱት ሰነዶች እምነት፣ ከባድ ስደትንና የሞት ማስፈራሪያን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጥ በግልጽ ያስረዳሉ። ማኅደሩ የሚያስተላልፈውን ትልቅ ትርጉም ያለው መልእክት ሰዎች ሊገነዘቡ የሚችሉት በይሖዋ ምሥክሮች ሙዚየሞች ውስጥ ከተቀመጠ ብቻ ነው።
ከኩሰሮ ልጆች መካከል እስከ ቅርብ ጊዜ በሕይወት የቆየው ፖል ጌርሃርት ኩሰሮ ሲሆን እሱም ጥቅምት 2022 ሕይወቱ አልፏል። ወታደራዊ ሙዚየሙ የእህቱን ኑዛዜ ሲያከብር ለማየት ይጓጓ ነበር፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይህ እንዲፈጸም ለማድረግ በይፋ ጥረት ያደርግ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞቼ የሞቱት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው። ስለዚህ ማኅደሩ፣ ካልጠፋ ቦታ በወታደራዊ ሙዚየም ውስጥ መቀመጡ ተገቢ እንደሆነ አይሰማኝም።”
የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ሙዚየሙ በግልጽ የተቀመጠውን የአነማሪን ኑዛዜ አለማክበሩ ዓይን ያወጣ የፍትሕ መጓደል ነው። የኩሰሮ ቤተሰብ ፍላጎት ቀደም ሲል በናዚ አገዛዝ ተጥሶ ነበር፤ በዘመናዊቷ ጀርመንም ይኸው ሁኔታ እየተደገመ ነው።
የሚያሳዝነው ማኅደሩም ቢሆን የሚገባውን አክብሮት አላገኘም። በውስጡ ከተካተቱ ከ1,000 የሚበልጡ ሰነዶች መካከል ለእይታ የቀረቡት 6ቱ ብቻ ናቸው፤ የቀሩት በሙሉ ከሕዝብ እይታ ውጭ በሙዚየሙ መጋዘን ውስጥ ተቀምጠዋል።
ፍርድ ቤቱ ማኅደሩን ሕጋዊና ትክክለኛ ባለቤቶቹ ለሆኑት ለይሖዋ ምሥክሮች እንዲያስረክብ እንጸልያለን።—ሉቃስ 18:7