በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት አና ዴንትስ እና ወንድም ኤሪክ ፍሮስት፤ በጀርመን የሚገኘው የባዴን ዉርተምበርግ ምክር ቤት

የካቲት 22, 2021
ጀርመን

የጀርመን ክልላዊ ምክር ቤት የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጭቆና በድፍረት መቋቋማቸውን ዘከረ

የጀርመን ክልላዊ ምክር ቤት የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጭቆና በድፍረት መቋቋማቸውን ዘከረ

የባዴን ዉርተምበርግ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑትን ሙቴሬም ኧራስን የሚያሳይ ፎቶግራፍ፤ በኢንተርኔት ከተላለፈው ፕሮግራም የተወሰደ

በጀርመን የሚገኘው የባዴን ዉርተምበርግ ምክር ቤት፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሞቱትን የናዚ አገዛዝ ሰለባዎች ለመዘከር ጥር 27, 2021 ያከበረው ዓመታዊ መታሰቢያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያተኮረ ነበር። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ሥነ ሥርዓቱ የተከናወነው በኢንተርኔት አማካኝነት ነው። በስዊዘርላንድ፣ በኔዘርላንድስ፣ በኦስትሪያ እና በጀርመን የሚኖሩ ከ37,000 የሚበልጡ ሰዎች በፕሮግራሙ ላይ ታድመዋል። በተጨማሪም ፕሮግራሙ በቪዲዮ ተቀርጾ ኢንተርኔት ላይ የተጫነ ሲሆን ይህ ቪዲዮ 78,000 ጊዜ ያህል ታይቷል።

የባዴን ዉርተምበርግ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሙቴሬም ኧራስ እንደገለጹት “የይሖዋ ምሥክሮች ስለደረሰባቸው ስደት የሚያወሳ በቂ መረጃ አለ፤ . . . ሆኖም ታሪኩ በብዙኃኑ ዘንድ አይታወቅም።” ፕሬዚዳንቷ አክለው እንደተናገሩት በዚያ የጨለማ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ያሳለፉት ሕይወት “ጥላቻንና መድሎን መቋቋም እንዲሁም . . . ከዓመፅ መራቅ ስለሚቻልበት መንገድ በአሁኑ ዘመን ላለነው ግሩም ትምህርት ይዞልናል።”

ፕሬዚዳንት ሙቴሬም ኧራስ፣ የእህት አና ዴንትስን ታሪክ ጠቅሰዋል፤ አና የምትኖረው በሎራክ፣ ባዴን ዉርተምበርግ ነበር። የአና ወላጆች የሞቱት በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ነው። አና በትምህርት ቤት “ሃይል ሂትለር” የሚለውን ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረችም። ውሎ አድሮ በእምነት አጋሮቿ እርዳታ ወደ ስዊዘርላንድ ሸሸች። ከጊዜ በኋላ አና ከባለቤቷ ጋር በዩናይትድ ስቴትስ መኖር ጀመረች። ፕሬዚዳንት ሙቴሬም ኧራስ “አና ዴንትስ በድፍረት በአቋሟ ጸንታለች” ብለዋል፤ አክለውም “እንዲህ ያለ ብርታት የሰጣት እምነቷ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ዶክተር ሃንስ ሄሰ

የታሪክ ምሁር የሆኑት ዶክተር ሃንስ ሄሰ፣ ጀርመን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የታገዱት በ1933 ማለትም ናዚዎች ሥልጣን በያዙ በሁለት ወር ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል። ዶክተር ሄሰ፣ ወንድሞቻችን “በራሪ ወረቀቶችን በማሰራጨትና የስብከት እንቅስቃሴያቸውን በመቀጠል እገዳውን አለመቀበላቸውን” እንዳሳዩ ተናግረዋል።

እኚህ የታሪክ ምሁር የወንድም ጉስታፍ ሽታንጌን ተሞክሮ ጠቅሰዋል። ወንድም ሽታንጌ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት አቃቤ ሕጉ “ሁሉም ሰው እንደ አንተ ዓይነት አቋም ቢይዝ ምን ሊፈጠር ነው?” ሲለው ወንድማችን “እንደዚያ ቢሆንማ ኖሮ ጦርነቱ ወዲያውኑ ያቆም ነበር” በማለት መለሰለት።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ “እናንተ ምሥክሮች ወደፊት ግፉ!” የሚለው የመንግሥቱ መዝሙራችን ተላልፎ ነበር። በማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ አስተባባሪ የሆነው ወንድም ዎልፍራም ስሉፒና፣ የዚህን መዝሙር የመጀመሪያ ግጥም የጻፈው የሙዚቃ ባለሙያ የሆነው ወንድም ኤሪክ ፍሮስት እንደሆነ ተናግሯል፤ ወንድም ፍሮስት ይህን ሙዚቃ ያቀናበረው በ1942 በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ በነበረበት ወቅት ነው። ወንድም ፍሮስት በወቅቱ “በካምፑ ውስጥ የሚፈጸመው ግፍ ከአቅም በላይ በመሆኑ” አብረውት የነበሩትን እስረኞች ለማበረታታት በማሰብ መዝሙሩን እንዳቀናበረ ከአሥርተ ዓመታት በፊት ባደረገው ቃለ መጠይቅ ላይ ገልጾ ነበር።

የ13 እና የ15 ዓመት ወጣቶች የሆኑ ማራ ኬምፐር እና ፊን ኬምፐር የተባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለእህት ሲሞን አርኖልድ ሊብስተር ቃለ መጠየቅ አድርገውላት ነበር፤ እህት ሊብስተር በናዚ አገዛዝ ወቅት የነበረች ሲሆን በልጅነቷ ከባድ ስደት ደርሶባታል። የናዚ አገዛዝን ለመደገፍ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ባለሥልጣናቱ ወደ ተሃድሶ ትምህርት ቤት ላኳት። ንጹሕ አቋሟን እንድታላላ የተደረገባትን ጫና በመቋቋሟ “ከፍተኛ ደስታ” እንደተሰማት ገልጻለች።

እህትና ወንድም የሆኑት ማራ እና ፊን በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለእህት ሲሞን አርኖልድ ሊብስተር ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉላት

ይህ ሥነ ሥርዓት፣ በከባድ ስደት ወቅት አስተማማኝ ረዳት ስለሆነው ስለ ይሖዋ ብዙዎች እንዲያውቁ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ስለከፈተ በጣም ደስ ብሎናል።—ዕብራውያን 13:6