ግንቦት 17, 2023
ጀርመን
ፍሎስንበርግ ማጎሪያ ካምፕ ለይሖዋ ምሥክሮች መታሰቢያ አስመረቀ
በባቬሪያ፣ ጀርመን የሚገኘው ፎሎስንበርግ ማጎሪያ ካምፕ በዚያ ታስረው እያሉ ሕይወታቸው ላለፈ የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጀውን መታሰቢያ ሚያዝያ 22, 2023 አስመርቋል። ፎሎስንበርግ ለይሖዋ ምሥክሮች መታሰቢያ ካቆሙ የማጎሪያ ካምፖች ዘጠነኛው ነው።
በፎሎስንበርግና በአካባቢው ባሉ ካምፖች ከ100 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ታስረው ነበር። ከቤተሰባቸው አባላት አንዳንዶቹ በመታሰቢያው የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል። በቦታው የተገኘ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለማሰብ እንኳ የሚከብድ የጭካኔ ድርጊት በተፈጸመበት ቦታ በተዘጋጀ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት በጣም ያሳዝናል። ወንድሞቻችን ያሳዩትን ታማኝነት ማስታወሳችን ግን ይህን ሥነ ሥርዓት አስደሳችና ክብር የተላበሰ እንዲሆን አድርጎታል።”
የፎሎስንበርግ ማጎሪያ ካምፕ መታሰቢያ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር የርግ ስክሪበላይት “[ናዚ] መጋቢት 1933 ሥልጣን በያዘበት ወቅት መጀመሪያ የታገደው የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖት ነው” ብለዋል። ዳይሬክተሩ ባቀረቡት አጠር ያለ ንግግር ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “[የይሖዋ ምሥክሮች] እምነት በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ያጋጠማቸውን ሁኔታ ለመቋቋም ብርታትና ኃይል ሰጥቷቸዋል። . . . ይህ ብርታታቸው ከእነሱም አልፎ እምነታቸውን የማይጋሩ ሌሎች ሰዎችን ጠቅሟል።”
በጀርመን የይሖዋ ምሥክሮች ቃለ አቀባይ የሆነው ወንድም ውልፍራም ስሉፒና በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባቀረበው ንግግር ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በጀርመን በነበረው የጨለማ ጊዜ ውስጥ በሕሊናቸው በተመሩት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰው ግፍ ተረስቶ አለመቅረቱ ለሁላችንም ትልቅ ነገር ነው።”
በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ መከራ የደረሰባቸውና የተገደሉት እነዚህ ታማኝ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአምላክ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ውስጥ እንደሰፈሩ እርግጠኞች ነን።—ሚልክያስ 3:16