በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሂቶዮሺ ከተማ የተከሰተው ጎርፍ

ሐምሌ 23, 2020
ጃፓን

በደቡባዊ ጃፓን የተከሰተው ኃይለኛ ዝናብና ጎርፍ ከባድ ጉዳት አስከትሏል

በደቡባዊ ጃፓን የተከሰተው ኃይለኛ ዝናብና ጎርፍ ከባድ ጉዳት አስከትሏል

በሐምሌ 2020 መጀመሪያ አካባቢ የጣለው ከባድ ዝናብ በኪዩሹ፣ ጃፓን ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አስከትሏል። አደጋው በተለይ በኩማሞቶ ክፍለ ግዛት በሚገኙት የሚናማታ እና የሂቶዮሺ ከተሞች እንዲሁም በፉኩኦካ ክፍለ ግዛት በምትገኘው የኦሙታ ከተማ ውስጥ በሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ጉዳት አድርሷል። ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል በአደጋው ምክንያት የሞተ ባይኖርም አንድ ወንድምና አንዲት እህት ቀለል ያለ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም የተከሰተው ጎርፍ በ48 የወንድሞቻችን ቤቶችና በሁለት የስብሰባ አዳራሾች ላይ ጉዳት አስከትሏል። ሌሎች ሁለት የስብሰባ አዳራሾች ደግሞ በመሬት መንሸራተት ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ እርዳታ እንዲሰጥ ያቋቋመው የኪዩሹ ኦኪናዋ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አሁን በጎርፉ ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞችና እህቶች የሚደረገውን የእርዳታ ሥራ እያስተባበረ ይገኛል። በስፍራው ያሉ የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ተወካዮች እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራውን እየደገፉ ነው።

“ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው” አምላካችን ይሖዋ በዚህ አደጋ ለተጎዱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል እንጸልያለን።—ሮም 15:5