በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች በልዩ ዘመቻው ሲካፈሉ፦ (በስተ ግራ) ኦሳካ እና (በስተ ቀኝ ከላይና ከታች) ቶኪዮ

ሐምሌ 30, 2024
ጃፓን

ከሰባት አገራት የተውጣጡ የይሖዋ ምሥክሮች በኦሳካ እና በቶኪዮ፣ ጃፓን ልዩ የስብከት ዘመቻ አካሄዱ

ከሰባት አገራት የተውጣጡ የይሖዋ ምሥክሮች በኦሳካ እና በቶኪዮ፣ ጃፓን ልዩ የስብከት ዘመቻ አካሄዱ

ከግንቦት 13 እስከ ሰኔ 2, 2024 ባሉት ቀናት በጃፓን የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ልዩ የስብከት ዘመቻ ተካፍለዋል፤ ዘመቻው የተካሄደው ኦሳካ እና ቶኪዮ በተባሉት የጃፓን ከተሞች ውስጥ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ነው። በተጨማሪም ከኒው ዚላንድ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጀርመንና ከፈረንሳይ 350 ያህል የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ዘመቻ እንዲያግዙ ተጋብዘው ነበር።

ቶኪዮ እና ኦሳካ በድምሩ ከ15 ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች አሏቸው። በጃፓን ያሉ ወንድሞችና እህቶች ከሌላ አገር ከመጡት ጋር ሆነው በተለያዩ የአደባባይ ምሥክርነት ዘርፎች ተካፍለዋል። ከሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት ማድረግ የቻሉ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም አስጀምረዋል።

ከአውስትራሊያ የመጣች እህት ከአንዲት ጃፓናዊት እህት ጋር በዘመቻው ሲካፈሉ

አንዲት እህት በጋሪ ምሥክርነት እየተካፈለች ሳለ፣ የአምላክን ቃል ማጥናት የሚፈልግ ሰው ማነጋገር እንደምትፈልግ በመግለጽ ጸለየች። ብዙም ሳይቆይ አንድ ሰው ወደ ጋሪው መጣና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ማወቅ እንደሚፈልግ ገለጸ። ሰውየው የሚቀለው ቋንቋ ቻይንኛ በመሆኑ እህታችን ቻይንኛ የሚናገር አንድ ጃፓናዊ ወንድም እንዲያናግረው ሁኔታውን አመቻቸች። ሰውየው ከእህት ጋር መጀመሪያ ከተነጋገረ ከሁለት ቀን በኋላ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኘ።

አንዲት እህት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ያገኘቻት ሴት መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ ለመመልከት ተስማማች። ከዚያም “በዚህ ቪዲዮ ላይ ያሉት ጥያቄዎች ሁሉ የእኔም ጥያቄዎች ናቸው!” አለች። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በደስታ የተስማማች ሲሆን ከእህታችን ጋር ሆና በቀጣዩ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝታለች።

በኦሳካ የሚገኘው የሆንማቺ ጉባኤ ወንድሞችና እህቶች ከሌላ አገር ከመጡት ወንድሞችና እህቶች ጋር፤ ልዩ የስብከት ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት በተደረገ የእንኳን ደህና መጣችሁ ግብዣ ላይ

ይህ ዘመቻ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አብረው ጊዜ ለማሳለፍ ግሩም አጋጣሚም ፈጥሮላቸዋል። በታሱኖ፣ ጃፓን የምትኖረው የ20 ዓመቷ ኤካ እንዲህ ብላለች፦ “ፈጽሞ የማይረሳ ጊዜ ነው። ይሖዋ በዚህ ዘመቻ የመካፈል አጋጣሚ ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።” አኪሂሮ የተባለ አንድ ጃፓናዊ የጉባኤ ሽማግሌ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ከሌሎች አገራት ከመጡት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብረን ማገልገላችን በጣም አበረታቶናል። አገልግሎታችንን በጣም አስደሳች አድርጎልናል።”

በዚህ ልዩ ዘመቻ ለመካፈል እና ‘ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይሖዋን ለማወደስ’ ‘በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ላቀረቡት’ በርካታ ጃፓናውያን እንዲሁም ከሌሎች አገራት የመጡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ልባዊ ምስጋናችንን መግለጽ እንፈልጋለን።​—ዕዝራ 3:11፤ መዝሙር 110:3