በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከላይ በስተ ግራ፦ ወንድሞች በኑማዙ፣ ጃፓን በሚገኘው የቤቴል ሕንፃ ውስጥ በተገጠመው ማተሚያ መሣሪያ ላይ ሲሠሩ፣ 1972። ከላይ በስተ ቀኝ፦ በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የታተሙት የመጀመሪያዎቹ መጽሔቶች ተደርድረው። ከታች፦ በኤቢና፣ ጃፓን የሚገኘው የአሁኑ የማተሚያ ሕንፃ

ጥቅምት 4, 2022
ጃፓን

የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የሃምሳ ዓመት የሕትመት ታሪክ

የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የሃምሳ ዓመት የሕትመት ታሪክ

በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከናወነው የሕትመት ሥራ በ2022 ሃምሳ ዓመት አስቆጥሯል።

በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓመታት በጃፓን የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች 70 በሚሆኑ ሚስዮናውያን ታግዘው በትጋት ያከናወኑት የስብከት ሥራ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ጭማሪ እንዲገኝ አድርጓል። በመሆኑም በጃፓንኛ የሚዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ተፈላጊነት እየጨመረ ሄደ፤ ይህን ፍላጎት ለማሟላት የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲያትም ተወሰነ።

ጥቅምት 1969 “ሰላም በምድር ላይ” በሚል ጭብጥ ቶኪዮ ውስጥ በተካሄደው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ወንድም ናታን ኖር ተገኝቶ ነበር፤ ወንድም ኖር በፉጂ ተራራ ግርጌ፣ ኑማዙ በተባለው ቦታ ማተሚያዎች ያሉት አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚገነባ አስታወቀ።

በኑማዙ፣ ጃፓን የሚገኘው የቤቴል ማተሚያ ቤት እንደተከፈተ አካባቢ ወንድሞች ማተሚያ ፕሌት ሲያዘጋጁ

ጥር 1972 ግንባታው ተጀመረ። ነሐሴ 15, 1972 መጠረዣና መቁረጫ የተሟላለት 40 ቶን የሚመዝን ማተሚያ መሣሪያ ተገጠመ። በጃፓንኛ የወጣው የጥቅምት 8, 1972 ንቁ! በዚህ ቅርንጫፍ ቢሮ የታተመው የመጀመሪያው መጽሔት ነበር። ማተሚያው ላይ ይሠራ የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ትዝታውን ተናግሯል፦ “ከማተሚያው የወጡ አዳዲስ መጽሔቶች በካርቶን በካርቶን ተከምረው ሳይ ከደስታዬ ብዛት የተነሳ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም።”

በ1982 የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ በኤቢና ወደተገነቡት አዳዲስ የቤቴል ሕንፃዎች ተዛወረ። አዲሱ ሕንፃ በኑማዙ ከነበረው ሦስት እጥፍ ይሰፋል፤ ማተሚያና መጠረዣ መሣሪያዎቹም ዘመናዊና ፈጣን ናቸው። ቅርንጫፍ ቢሮው ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔት በተጨማሪ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን ማተም ጀመረ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማተም ጀመረ።

ወንድሞች ዘመናዊ በሆነው ማተሚያ መሣሪያ ላይ የቀለም ልኩን ሲያስተካክሉ የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ፎቶግራፍ፤ ኤቢና፣ ጃፓን

የጃፓን ማተሚያ በአሁኑ ወቅት በየወሩ 13.2 ሚሊዮን መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ያትማል። ከ2013 ወዲህ ደግሞ ከ100 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በዚህ ቅርንጫፍ ቢሮ ታትመው በዓለም ዙሪያ ከ50 ወደሚበልጡ አገሮች ተልከዋል።

በ1972 ጃፓን ውስጥ 13,000 አስፋፊዎች ነበሩ። ከሃምሳ ዓመት በኋላ ማለትም በ2022 የአስፋፊዎች ቁጥር ከ213,000 በላይ ሆኗል። ይህ የሕትመት ቅርንጫፍ ቢሮ በጃፓንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ ምን ያህል እያገዘ እንደሆነ ስናይ በጣም እንደሰታለን።—ማቴዎስ 28:19, 20