ኅዳር 18, 2019
ጃፓን
ጃፓን ባውሎይ በተባለ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ ተመታች
ጥቅምት 25 እና 26, 2019 ባውሎይ የተባለ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ በጃፓን ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰ። ይህ ከባድ አውሎ ነፋስ ከመስከረም ወዲህ የጃፓንን ምሥራቃዊ ክፍል ካጠቁት ሃጊቢስ እና ፋክሳይ ከተባሉት ተከታታይ አውሎ ነፋሳት በኋላ የተከሰተ ነው። ባውሎይ በተባለው በዚህ አውሎ ነፋስ የተነሳ ወንዞች በጣም ሞልተው ወደ ውጭ በመፍሰሳቸው አካባቢው በጎርፍ ተጥለቅልቋል። ቢያንስ 81 የሚሆኑ የወንድሞቻችን ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአደጋው ሕይወቱን ያጣ የይሖዋ ምሥክር እንዳለ ባይገለጽም አንዲት እህት ጉዳት ደርሶባታል። በቺባ ክፍለ ግዛት የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በእነዚህ ሦስት አውሎ ነፋሳት የተነሳ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል።
ሃጊቢስ እና ፋክሳይ በተባሉት አውሎ ነፋሳት ጉዳት የደረሰባቸውን ወንድሞች ሲረዱ የቆዩ ሦስት የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ነበሩ። እነዚህ ኮሚቴዎች በባውሎይ ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞቻችንም እርዳታ መስጠት ጀምረዋል። የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ፣ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለማሟላት የሚያደርጉትን ጥረት እየደገፈ ነው፤ ኮሚቴዎቹ አካባቢውን በማጽዳት፣ ከበሽታ አምጪ ተሕዋስያን በማጽዳትና የፈራረሱ ቤቶችን በመጠገን እርዳታ ያበረክታሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ደግሞ ወንድሞችንና እህቶችን ለማበረታታት የሚደረገውን ጥረት ያስተባብራሉ።
እንዲህ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ላጋጠማቸው በጃፓን የሚኖሩ ወንድሞቻችን እንጸልያለን፤ ይሖዋ በተከታታይ በተከሰቱት በእነዚህ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ “መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውን” ሰዎች እንደሚያጽናና እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 34:18