በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 6, 2023
ጆርጂያ

የማቴዎስ መጽሐፍ በሚንግራልኛ ቋንቋ ወጣ

የማቴዎስ መጽሐፍ በሚንግራልኛ ቋንቋ ወጣ

ሰኔ 30, 2023 የጆርጂያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆኒ ሻላምቤሪድዜ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በሚንግራልኛ መውጣቱን አበሰረ። የማቴዎስ ወንጌል በዚህ ቋንቋ የታተመው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የወጣው “በትዕግሥት ጠብቁ”! በተባለው የ2023 የክልል ስብሰባ ላይ ነው፤ ስብሰባው የተደረገው በዙግዲዲ፣ ጆርጂያ ባለ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ 627 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። መጽሐፉ በታተመም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ወዲያውኑ ወጥቷል።

ሚንግራልኛ በዋነኝነት የሚነገረው በምዕራብ ጆርጂያ በሚገኘው በሳሜግሬሎ ክልል ውስጥ ነው። በ2019 የይሖዋ ምሥክሮች በዙግዲዲ የርቀት የትርጉም ቢሮ አቋቋሙ።

የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሚንግራልኛ ጽሑፎችን ካዘጋጁ ጥቂት ድርጅቶች መካከል ይገኙበታል። አንድ ተርጓሚ “ሚንግራልኛ በዋነኝነት የንግግር ቋንቋ ስለሆነ ወጥ የሆነ የሰዋስውም ሆነ የአጻጻፍ ሕግ የለውም” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ፈታኝ የሆነብን ነገር ይህ ነው። በመጨረሻ ግን ሚንግራልኛ ለሚነገርበት መንገድ በደንብ ትኩረት እየሰጠን የጆርጂያኛን የሰዋስው ሕግ እንጠቀም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን።”

በዙግዲዲ፣ ጆርጂያ የሚገኘው የሚንግራልኛ የርቀት የትርጉም ቢሮ

በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ቃላት በሚንግራልኛ አቻ ትርጉም የላቸውም። ለምሳሌ በሚንግራልኛ “ንስሐ መግባት” የሚል ቃል የለም። በመሆኑም ተርጓሚዎች ሐሳቡን “በፈጸሙት ስህተት ማዘን” ብለው ተርጉመውታል።

ሚንግራልኛ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ” ተጨማሪ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችላቸውን ይህን አዲስ ትርጉም ማግኘት በመቻላቸው በጣም ተደስተናል።—ማቴዎስ 5:6