በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 25, 2023
ግሪክ

ከሳሽ ኮኪናኪስ እና ተከሳሽ ግሪክ፦ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያሳለፈው ጉልህ ውሳኔ ከ30 ዓመት በኋላም ትልቅ ፋይዳ አለው

ውሳኔው በመላው አውሮፓ ሃይማኖታዊ መብቶች እንዲከበሩ መሠረት ጥሏል

ከሳሽ ኮኪናኪስ እና ተከሳሽ ግሪክ፦ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያሳለፈው ጉልህ ውሳኔ ከ30 ዓመት በኋላም ትልቅ ፋይዳ አለው

ግንቦት 25, 2023 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ በከሳሽ ኮኪናኪስ እና በተከሳሽ ግሪክ መካከል በነበረው ክርክር ላይ ያሳለፈው ውሳኔ 30ኛ ዓመቱን አስቆጠረ፤ የሕግ ባለሙያዎች ፍርድ ቤቱ ካሳለፋቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ውሳኔዎች አንዱ ይህ እንደሆነ ይናገራሉ። ፍርድ ቤቱ፣ አንዲት አገር የግለሰቦችን ሃይማኖታዊ መብት ጥሳለች የሚል ውሳኔ ሲያሳልፍ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር። ውሳኔው የአውሮፓ ምክር ቤት አባል በሆኑት 46 አገራት ውስጥ ከ1993 ወዲህ ሃይማኖታዊ መብትን በማስከበር ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። እንደ ሩሲያ ያሉ አንዳንድ ኃያላን አገራት እምነታችንን በይፋ የመግለጽ መብታችንን ለመጋፋት በሚጥሩበት በአሁኑ ወቅት ከኮኪናኪስ ጋር በተያያዘ የተላለፈው ውሳኔ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠቀሜታ አለው።

እስከ ዛሬም ድረስ የአውሮፓ ምክር ቤት ይፋዊ ድረ ገጽ፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት ስለሚያስገኘው ጥበቃ ሲገልጽ የኮኪናኪስን ጉዳይ ይጠቅሳል። ይህ ጉዳይ በሕግ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለማስተማሪያነት ጥቅም ላይ የሚውል ከመሆኑም ሌላ ለአውሮፓ ፍርድ ቤት በሚቀርቡ ይግባኞች ላይም ይጠቀሳል።

ከኮኪናኪስ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተላለፈው ውሳኔ “በቃልም ሆነ በተግባር [ስለ እምነት] መመሥከር ከሃይማኖታዊ እምነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ” መሆኑን ግልጽ በማድረጉ ይታወቃል። ውሳኔው “እምነትን በይፋ የመግለጽ ነፃነት፣ . . . ሌሎች ሰዎችን ለማሳመን የመሞከር መብትን ለምሳሌ ‘ማስተማርን’” እንደሚያካትት አረጋግጧል።

ይህን ጉዳይ ከተመለከቱት ዘጠኝ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ዳኞች አንዱ የሆኑት ዳኛ ደ ማየር እንዲህ ብለዋል፦ “‘እምነትን የማሰራጨት ቅንዓት’ የሚል ፍቺ የተሰጠው ‘ሃይማኖትን ማስቀየር’ የሚያስቀጣ ሊሆን አይችልም፤ ሃይማኖትን ማስቀየር ‘አንድ ሰው ሃይማኖቱን የሚገልጽበት’ ፍጹም ሕጋዊ የሆነ መንገድ ነው።”

ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ወንድም ሚኖስ ኮኪናኪስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በፍርድ ቤት ያደረገው ሙግት ማብቂያ እንዲያገኝ አድርጓል። የግሪክ ባለሥልጣናት፣ አምባገነኑ ኢዮአኒስ ሜታክሳስ ያወጣውን “ሃይማኖትን ማስቀየር” ወንጀል እንደሆነ የሚደነግገውን ሕግ ጥሰሃል በማለት ወንድም ሚኖስን በ1938 በቁጥጥር ሥር አዋሉት። በወቅቱ የ30 ዓመት ጎልማሳ የነበረው ወንድም ሚኖስ ይህን ሕግ መሠረት በማድረግ ከ1938 እስከ 1992 ባሉት ዓመታት ከታሰሩት 19,147 የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያው ነው። በእነዚህ አሥርተ ዓመታት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በደልና እንግልት ይደርስባቸው እንዲሁም የኃይል ጥቃት ይሰነዘርባቸው ነበር።

ወንድም ሚኖስ ግን በዚህ ሳይበገር አገልግሎቱን ማከናወኑን ቀጠለ። በዚህ ምክንያት ከ60 ጊዜ በላይ በቁጥጥር ሥር ውሏል፤ 18 ጊዜ በግሪክ ፍርድ ቤቶች ቀርቧል፤ ከስድስት ዓመት በላይ በእስር ቤቶችና በግዞት አሳልፏል እንዲሁም በተደጋጋሚ መቀጮ ከፍሏል።

በመጨረሻም በ1993 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ ወንድም ሚኖስ ጥፋተኛ እንዳልሆነና የግሪክ መንግሥት ሃይማኖታዊ መብቱን እንደተጋፋ የሚገልጽ ብይን አስተላለፈ፤ በዚህ ጊዜ ወንድም ሚኖስ 84 ዓመቱ ነበር። ፍርድ ቤቱ ወንድም ሚኖስ ለብዙ ዓመታት ለደረሰበት መከራ እንዲሁም በፍርድ ቤት ክርክር ላወጣው ወጪ ካሳ እንዲከፈለው ትእዛዝ አስተላለፈ። ወንድም ሚኖስ ቀሪውን ሕይወቱን ያሳለፈው በቀርጤስ ነው። በ1999 በ90 ዓመቱ በሞት አንቀላፋ።

ዳኛ ደ ማየር፣ ተከሳሹ ኮኪናኪስ ወንጀለኛ እንዳልሆነ ገልጸዋል፤ “የተፈረደበት መጥፎ ባሕርይ ኖሮት ሳይሆን [እምነትን የማሰራጨት] ቅንዓት ስላሳየ ብቻ ነው” ብለዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ጠበቃ የሆነው ፊሊፕ ብረምሊ፣ ይህ ጉልህ ውሳኔ በዛሬው ጊዜ ላሉ የሕግ ጉዳዮች ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግሯል። “ከኮኪናኪስ ጋር በተያያዘ የተላለፈው ውሳኔ፣ ሰዎች ስለ እምነታቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሌሎች የመናገር መብታቸው እንዲረጋገጥ አድርጓል። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከሃይማኖታዊ ነፃነት ጋር በተያያዘ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሁሉ በተደጋጋሚ የሚጠቀስና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፤ ከአውሮፓ ውጭም እንኳ ይጠቀሳል።”

ከኮኪናኪስ ጋር በተያያዘ ለተገኘው ታላቅ ድልና ይህ ውሳኔ ለጣለው መሠረት ይሖዋን እናመሰግናለን። ‘ለምሥራቹ ስንሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ ስንጥር’ ለሚሰጠን ጥበብና አመራር ይሖዋን በእጅጉ እናመሰግነዋለን።—ፊልጵስዩስ 1:7