በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰኔ 19, 2023
ግሪክ

የማቴዎስ መጽሐፍ በሮማኒ (የደቡባዊ ግሪክ) ቋንቋ ወጣ

የማቴዎስ መጽሐፍ በሮማኒ (የደቡባዊ ግሪክ) ቋንቋ ወጣ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ሰኔ 10, 2023 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በሮማኒ (የደቡባዊ ግሪክ) ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። መጽሐፉ መውጣቱ የተነገረው በፓይሪየስ፣ግሪክ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ ነው። በመላው ግሪክና ቆጵሮስ ለሚገኙ ጉባኤዎች የተላለፈውን ይህን ፕሮግራም ከ29,000 የሚበልጡ ሰዎች ተከታትለውታል። ፕሮግራሙ እንደተጠናቀቀ መጽሐፉ በዲጂታል ፎርማት ተለቅቋል። በመጪዎቹ ወራት ጉባኤዎች የታተመውን ቅጂ ማግኘት ይችላሉ።

ሮማኒ (የደቡባዊ ግሪክ) በጽሑፍ የሰፈረ የሰዋስው ሕግ የለውም፤ ይህም የትርጉም ሥራውን ከባድ ያደርገዋል። የትርጉም ቡድኑ አሥር ተርጓሚዎችን ያቀፈ ሲሆን ሥራቸውን የሚያከናውኑት በግሪክ ቅርንጫፍ ቢሮ ነው። ከመስክ ሆነው በርቀት የሚሠሩ ወንድሞችና እህቶችም ለትርጉም ቡድኑ ድጋፍ ያደርጋሉ።

አንዲት እህት የማቴዎስን መጽሐፍ በሮማኒ (የደቡባዊ ግሪክ) ቋንቋ ካነበበች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሁትና ስለ ይሖዋ የተማርኩት በግሪክኛ ነው። የማነበውንና የምሰማውን ነገር ለመረዳት ባልቸገርም መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ማንበቤ ስሜቴ ይበልጥ እንዲነካና ለተግባር እንድነሳሳ አድርጎኛል።”

ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ማቴዎስ 26:38, 39 በሮማኒ (የደቡባዊ ግሪክ) የተተረጎመበት መንገድ ልቤን በጣም ነክቶታል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ’ ብሏቸው ነበር። ሆኖም ወደ ይሖዋ በመጸለይ የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠው ጠይቋል። ይህን ጥቅስ በደንብ መረዳቴ፣ አልፎ አልፎ ሐዘን ቢሰማኝ ስህተት እንዳልሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል። በተጨማሪም ይሖዋ ብርታት እንዲሰጠኝ አጥብቄ መጸለይና የሚሰማኝን ስሜት ለወንድሞቼና ለእህቶቼ ማካፈል እንዳለብኝ አስተምሮኛል።”

የሮማኒ (የደቡባዊ ግሪክ) ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ የሚረዳቸውን ይህን ውድ ስጦታ በማግኘታቸው ከእነሱ ጋር አብረን እንደሰታለን።—ያዕቆብ 4:8