በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ በ1920 ግሪክን በጎበኘበት ወቅት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችን ፓርተኖን በተባለው ቦታ ሲያነጋግር። ባለፉት ዓመታት ቅርንጫፍ ቢሮው የተከፈተባቸው የተለያዩ ቦታዎች፦ በአቴንስ የተከፈተው የመጀመሪያው ቢሮ (ከላይ)፣ ማሩሲ ውስጥ የነበረው ቢሮ (መሃል) እና በድራፔጾና የሚገኘው የአሁኑ ቅርንጫፍ ቢሮ

መስከረም 29, 2022
ግሪክ

የግሪክ ቅርንጫፍ ቢሮ 100 ዓመት አስቆጠረ

የግሪክ ቅርንጫፍ ቢሮ 100 ዓመት አስቆጠረ

ጥቅምት 6, 2022 የግሪክ ቅርንጫፍ ቢሮ ከተከፈተ 100 ዓመት አስቆጥሯል።

ወንድም ራዘርፎርድ ግሪክ ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲከፈት የጻፈው ደብዳቤ፣ ጥቅምት 6, 1922

የስብከቱ ሥራ በዘመናዊቷ ግሪክ የጀመረው በ1905 ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ወዲያውኑ በመላ አገሪቷ ተዳረሰ፤ ከዚያም በ1922 ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ በአቴንስ የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ ቢሮ አቋቋመ። ወንድም አታናሲዮስ ካራናሲዮስ የመጀመሪያው የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ ሆኖ ተሾመ። ቅርንጫፍ ቢሮው በ1936 ጽሑፎችን በግሪክኛ ማተም ጀመረ። ከሁለት ዓመት በኋላ የግሪክ መንግሥት ሃይማኖት ማስቀየርን የሚከለክል ሕግ አወጣ። ይህን ተከትሎም ወንድም ካራናሲዮስ በ1939 ታሰረ። ማተሚያው ተዘጋ፤ የድርጅቱ ንብረቶችም ለተወሰኑ ወራት ታገዱ። በኋላ ላይ ግሪክ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ስትገባ አገሪቱ በወታደራዊ ሕግ መተዳደር ጀመረች፤ በዚህም የተነሳ ጽሑፎቻችን ታገዱ እንዲሁም የቤቴል ሕንፃዎች ታሸጉ።

ጦርነቱ በ1945 ካበቃ በኋላ እገዳው ተነሳ፤ የስብከቱን ሥራ የሚመሩት ወንድሞችም ሥራውን እንደገና ማደራጀት ቻሉ። ከሁለት ዓመት በኋላ ወንድም ናታን ኖር የግሪክ ወንድሞችን ጎበኘ፤ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ በቴኔዱ ጎዳና፣ አቴንስ እንዲከፈትም ዕቅድ አወጣ። ይሖዋ ሥራውን ለማደራጀት የተደረጉትን ጥረቶች እንደባረከ በግልጽ ታይቷል። በ1951 በአገሪቱ 3,368 አስፋፊዎች ነበሩ፤ ይህም ከቀደመው ዓመት የ26 በመቶ ጭማሪ ነበረው።

ጥቅምት 1954 አቴንስ ውስጥ ካርታሊ ጎዳና ላይ የሚገኝ አዲስ የቤቴል መኖሪያ ሕንፃ ተወሰነ። ስደት ቢኖርም የስብከቱ ሥራ እየተስፋፋ ሄደ። በ1967 ግሪክ ውስጥ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሄደ፤ ይህን ተከትሎም በጉባኤ ስብሰባዎችና በስብከቱ ሥራ ላይ እንደገና እገዳ ተጣለ።

በእገዳው ወቅት ወንድም ሚካሊስ ካሚናሪስ እና ባለቤቱ ኤሌፍቴሪያ በቤቴል ያገለግሉ ነበር። ወንድም ካሚናሪስ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “በእገዳው ወቅት ቤቴል ውስጥ የሚካሄደው የሕትመት ሥራ ቆሞ ነበር፤ በመሆኑም በአቴንስ ከተማ ዳርቻ አካባቢ የሚገኘው ቤታችን እንደ ማተሚያ ቤት ማገልገል ጀመረ። ኤሌፍቴሪያ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶችን ትተይባለች፤ የምትጠቀምበት የጽሕፈት መሣሪያ አስቸጋሪ ነበር። በመጀመሪያ አስር ወረቀቶችን የጽሕፈት መሣሪያው ውስጥ አንድ ላይ ታስገባለች፤ እንደዚያም ሆኖ ቁልፎቹን በኃይል ካልተጫነች ፊደሎቹን መጻፍ አትችልም። እኔ ደግሞ ገጾቹን እየሰበሰብኩ እሰፋቸዋለሁ። በየቀኑ እስከ እኩለ ሌሊት ይህን ስንሠራ እናመሻለን። ከእኛ ቤት በታች አንድ ፖሊስ ይኖር ነበር፤ አንድም ቀን ግን ጠርጥሮን የማያውቅ መሆኑ ሁሌም ይገርመናል።”

እገዳው እያለም የአስፋፊዎች ቁጥር መጨመሩን ቀጠለ። በ1974 እገዳው ሲነሳ ተለቅ ያለ ቅርንጫፍ ቢሮ አስፈለገ። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት የግሪክ አስፋፊዎች ቁጥር ስለጨመረ በቅርንጫፍ ቢሮው ላይ የማስፋፊያ ሥራ ማከናወን የግድ ሆኗል። በድራፔጾና፣ ፓይሪየስ የሚገኘው የአሁኑ ቅርንጫፍ ቢሮ የተወሰነው ኅዳር 18, 2018 ነው። በአሁኑ ወቅት ግሪክ ውስጥ 27,752 አስፋፊዎች አሉ።

ባለፉት 100 ዓመታት ግሪክ ውስጥ የተለያዩ እገዳዎች፣ ጦርነቶችና ስደት እያለም የአስፋፊዎች ቁጥር መጨመሩ አንድ የሚያረጋግጠው ነገር አለ፤ ይሖዋ ‘ሥራውን በራሱ ጊዜ እንዳያፋጥን’ ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም።—ኢሳይያስ 60:22